ዴንማርክ በኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ያላትን ድጋፍ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

You are currently viewing ዴንማርክ በኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ያላትን ድጋፍ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

AMN- ጥቅምት 16/2019 ዓ.ም

ዴንማርክ በኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ያላትን ድጋፍ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሱን ክሮግስትረፕ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ዕውቀትና ቴክኖሎጂን ለመለዋወጥ ወሳኝ መድረክ መሆኑንም ጠቁመዋል።

3ኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት “ለውሃና ኢነርጂ ዋስትና የተጠበቀለት የወደፊት ሁኔታ ሳይንሳዊ መሠረት ያላቸውን ፖሊሲዎችና አጋርነቶችን ማሳደግ” በሚል መሪ ሐሳብ መካሄድ ጀምሯል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሱን ክሮግስትረፕ፣ የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ዕውቀትን ለመለዋወጥ፣ ልምድን ለመካፈል፣ የፈጠራ ሥራዎችን ለማስተዋወቅና ትብብርን ለማጠናከር እያገለገለ የሚገኝ መድረክ ነው ብለዋል።

ዴንማርክ በልማት ትብብር ፕሮግራሞቿና ተነሳሽነቶቿ አማካይነት የኢትዮጵያን የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ለመደገፍ የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት እንዳላት ተናግረዋል።

ከእነዚህም መካከል በውሃና ኢነርጂ ተቋማት መካከል በቀጥታ የልምድ ልውውጥ፣ የአቅም ግንባታ ማካሄድ፣ ብሔራዊ ፕሮግራሞችን መደገፍ፣ እንዲሁም የኢነርጂ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት ይገኙበታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች ጉልህ የልማት ዕድሎች እንዳሏት ገልጸዋል።

በዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ዘላቂ ኢንቨስትመንት፣ ፈጠራ፣ አስተማማኝ መረጃ፣ ጠንካራ ተቋማትና በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል የተጠናከረ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ያሉ መድረኮች እጅግ አስፈላጊ የሆኑት ለዚሁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያና በዴንማርክ መካከል ያለው ትብብር ከልማት ድጋፍ በላይ ለንግድ አጋርነት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ለፈጠራ እና ለግል ኢንቨስትመንት ዕድሎችን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

ዴንማርክ የጋራ ዓላማዎቻችንን ለማሳካት ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከልማት አጋሮች፣ ከግሉ ዘርፍና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መሥራቷን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የሩዋንዳ አምባሳደር ቻርለስ ካራምባ በበኩላቸው፣ ውሃና ኢነርጂ ለሰው ልጆች ደህንነት፣ ለኢኮኖሚ ልማት እና ለአካባቢ ዘላቂነት አስፈላጊ ሀብቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ ሁለት ሀብቶች በጥልቅ የተሳሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ ሀብቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ ቢኖራቸውም፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በኢኮኖሚና በሕዝብ ቁጥር ዕድገት እንዲሁም ከዘላቂነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ምክንያት እየጨመረ የመጣ ጫና እየተጋፈጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ውሃንና ኢነርጂን በብቃት፣ በታዳሽነትና በዘላቂነት ማስተዳደር የውሃ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የኢነርጂ ተደራሽነትን ለማስፋፋትና ተግዳሮቶችን መቋቋም የሚችል የወደፊት ሁኔታ ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት የተሻሉ ተሞክሮዎችን ለመካፈል፣ አዳዲስ ፈጠራዎችን ለማስተዋወቅና በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመመርመር ዕድል እንደሚሰጥ ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review