የመደመር መንግሥት በከተሞች ልማት ያከናወናቸው ተግባራት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ችለዋል

AMN- ጥቅምት 16/2019 ዓ.ም

የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት በከተሞች ልማት፣ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ እና በመኖሪያ ቤት ግንባታ ዘርፍ ያከናወናቸው ተግባራት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን ገለጹ።

የ2026 የዓለም የከተሞች ቀን “ከተማን ማደስ በኢትዮጵያ ከተሞች፤ ለሁሉም የሚተርፍ በቂ መኖሪያ ቤት” በሚል መሪ ሀሳብ በተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል።

መድረኩ በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በዩኤን ሀቢታት በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ትኩረቱንም በከተሞች እድገት፣ በመኖሪያ ቤት አቅርቦት እና በከተማ ማደስ ስራዎች ዙሪያ አድርጓል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን፣ የመደመር መንግሥት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከተሞች ልማትና በመኖሪያ ቤት ግንባታ ያከናወናቸው ተግባራት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።

ከተሞች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ የፈጠራ ሥራዎች፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማህበራዊ ትስስር ማዕከላት እንዲሆኑ በትኩረት መሰራቱንም ገልፀዋል።

በተለይም በልዩ ትኩረት እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል የቤት ልማት ዋነኛው መሆኑን ጠቁመው፣ በመደመር መንግሥት እውን እየሆነ ያለው የ1.5 ሚሊየን የመኖሪያ ቤት ግንባታ ለዚህ አብነት ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከናወኑት የኮሪደር ልማቶች እና የከተማ ማደስ ስራዎች ከተሞቻችን ንጹህ፣ ለኑሮ ምቹ እና ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት የሰጡ እንዲሆኑ አድርገዋል።

ይህም ከተሞቹ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ሳቢነት አቅም እንዲኖራቸው ማስቻሉን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

እነዚህና መሰል ስራዎች በዘርፉ እምርታዊ ለውጥ እንዲመጣ ትልቅ እድል ፈጥረዋል ብለዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም፣ ከልማት አጋሮች፣ ከግሉ ዘርፍ እና ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን አጋርነት በማጠናከር የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የከተማ ልማት ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠልም ለዜጎቿ ምቹ የሆነችና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አፅንኦት መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review