AMN- ጥቅምት 18/2019 ዓ.ም
የተማሪዎች ምገባን የበለጠ ለማስፋፋት፣ ደህንነቱንና ጥራቱን በመጠበቅ ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ በመርሀ ግብሩ የአደረጃጀት ለውጥ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
በተማሪዎች ምገባ የተደረገውን የአደረጃጀት ለውጥ ምክንያት በማድረግ ከመጋቢ ማህበራት ሰብሳቢዎች፣ የምገባ ዘርፉን ከሚያስተባብሩ የክፍለ ከተሞች አስተባባሪዎችና ባለድርሻዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፤ በየትምህርት ቤቱ ተግባራዊ ተደርጎ በተማሪዎች ውጤትና ስነ-ምግባር መሻሻል ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ የሚገኘው የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ስኬታማ እንዲሆን መጋቢ እናቶች እያበረከቱ የሚገኘው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መርሐ ግብሩ ለወላጆች እፎይታ ከመስጠቱ ባሻገር አዲስ አበባ ከተማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና እንድታገኝ ማስቻሉንም አመላክተዋል።
የተማሪዎች ምገባን የበለጠ ለማስፋፋት፣ ደህንነቱንና ጥራቱን በመጠበቅ ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ በመርሀ ግብሩ የአደረጃጀት ለውጥ መደረጉንም ጠቅሰዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲቀርብና የመጋቢ እናቶች ተጠቃሚነትን ለማሻሻል ወቅታዊ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ ከፍተኛ በጀት መድቦ የዋጋ ማሻሻያ ማድረጉን በመግለጽ በየትምህርት ቤቱ የተደራጁ ማህበራት በተዘጋጀው ሜኑ መሰረት በማቅረብ የምገባ አገልግሎቱ ውጤታማ እንዲሆን በከፍተኛ ኃላፊነት እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አማካሪና የዘርፉ አስተባባሪ አቶ ጥላሁን ፍቃዱ በበኩላቸው፤ በከተማ አስተዳደሩ በ2019 ዓ.ም ከ14 ሺህ በላይ እናቶች ተደራጅተው ከ1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ምግብ በነጻ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በአዋጅ ቁጥር 94/2019 ዓ.ም በተሰጠው ስልጣን መሰረት በየትምህርት ቤቱ በመገኘት የምገባ ፕሮግራሙን ውጤታማነት በሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር የሚያረጋግጥ መሆኑንም አመላክተዋል።
በንጉሱ በቃሉ