AMN ሐምሌ 7/2018 ዓ.ም

ጽንፈኝነት ፤ ዘረኝነት እና ጎጠኝነት የአንድን ማህበረሰብ ሰላም ፣ አንድነትና እድገት በእጅጉ ከሚያናጉ አደገኛ አስተሳሰቦች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡
እነዚህ ሁለቱ ከፋፋይ ባህሪያት እርስ በእርሳቸው የሚመጋገቡ ሲሆኑ፣ ማህበራዊ ትስስርን ከማናጋት ጀምሮ በሀገርና በህዝብ ላይ የተለያዩ አደጋዎችን ያስከትላሉ፡፡
የጽንፈኝነትና የጎጠኝነት እሳቤዎች ሰዎችን በጋራ ማንነታቸው ከማየት ይልቅ በብሄር ፣ በሃይማኖት ወይም በቡድን በመክፈል በመካከላቸው የጥላቻና የጥርጣሬ ግንብ እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡
ልዩነቶችን በውይይትና በንግግር ከመፍታት ይልቅ፣ የእኔ ሃሳብ ወይም የእኔ ቡድን ብቻ ትክክል ነው የሚል ግትርነት ያለው አቋም ስለሚከተሉ አብሮ የመኖር እሴትን ይሸረሽራሉ፡፡
ጽንፈኝነት ሃሳብን በኃይል ለመጫን ስለሚሞክር ወደ ግጭት እና ጦርነት የማምራት እድሉ ሰፊ ሲሆን ፤ በዚሁ በጽንፈኝነትና ጎጠኝነት ምክንያት ዜጎች ሕይወታቸውን እስከማጣት ፤ ከቄያቸው እስከመፈናቀል እና ንብረት እስከመውደም ሊደርስ ይችላል፡፡
ጽንፈኛና ጎጠኛ እሳቤዎች ከህግና ከጋራ ተጠቃሚነት ይልቅ ለቡድን ጥቅምና ፍላጎት ቅድሚያ የሚሰጡ በመሆናቸው ሃገራዊ ልማትና ሰላምን በእጅጉ ይጎዳሉ፡፡
እሳቤዎቹ የጋራ የሆኑ ሃገራዊ ራዕይና ማንነትን እስከማጥፋት የሚደርሱ ሲሆኑ ፤ እያንዳንዱ ቡድን የራሱን ጥቅም ብቻ ለማስከበር የሚታገል በመሆኑ ሀገርን ወደ መበታተንና እና ወደ ትርምስ ሊመራ ይችላል።
ጥቂት የማይባሉ የአለም ሃገራት በዚሁ እሳቤ ምክንያት በልማት ወደ ኋላ ከመቅረታቸውም በላይ ለከፋ የሰላም እጦት መዳረጋቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ጽንፈኝነትና ጎጠኝነት የልማት እና የአንድነት ሳይሆን የጥፋትና የመጠፋፋት መንገድን የሚከተሉ በመሆናቸው የአንድን ማህበረሰብ እድገትና ልማት ወደ ኋላ ያስቀራሉ ፤ ሰላምን ይነሳሉ ፤ የሰዎችን ሰብአዊ ክብር እስከመጣስ ይደርሳሉ፡፡
ዛሬ ላይ ከማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ተገቢ ላልሆነ የፖለቲካ ትርፍ አልያም ሆን ብለዉ ግጭት ለመፍጠር በማሰብ የአንደኛዉ ብሔር ወይም ሃይማኖት ተከታይ መስለዉ በሌላዉ ብሔር ወይም ሃይማኖት ላይ ሃሰተኛና የጥላቻ ንግግሮችን የሚጠቀሙ ግለሰቦች እየተበራከቱ መምጣታቸዉም ጽንፈኛ፤ ዘረኛና የጥላቻ እሳቤዎች እንዲበራከቱ ምክንያት መሆናቸዉን ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
በጽንፈኛና ጎጠኛ እሳቤዎች ምክንያት በማህበረሰብና በሃገር ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጥፋት ለመከላከል ራስን ከነዚህ እሳቤዎች ነጻ ማድረግ ፤ በምትካቸው መቻቻልን ፣ እኩልነትንና ምክንያታዊነትን ማስፈን እንደሚገባ እነዚሁ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
ጽንፈኝነት፤ ዘረኝነትና ጎጠኝነት የትኛውንም የህብረተሰብ ክፍል የማይወክል ከአንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ብቻ የሚመነጭ ፤ ህዝብና ሃገርን የሚጎዳ ፤ ጤናማ ያልሆነ አደገኛ እሳቤ በመሆኑ ሁሉም ሰው ሌላውን ብቻ ከመውቀስ ይልቅ ራሱን ከዚህ አደገኛ እሳቤ ነጻ ሊያደርግ እንደሚገባዉ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
ለረጅም ዘመናት ፈዉስ ያላገኘዉ የጽንፈኝነት: ዘረኝነት: ጥላቻና የጎጠኝነት እሳቤ ሁሉን ተጠቃሚ በሚያደርግ በጋራ እሳቤ ካልተተካ ቤተሰብን: ማህበረሰብን: ተቋምን እና ሃገርን እስከማፍረስ የሚደርስ አደገኛ በሽታ ነዉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሰሞኑን በተካሄደው የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ “ኢትዮጵያውያን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በአንድ ድምፅ ጽንፈኝነትን ፣ ባንዳነትንና ዘረኝነትን አንፈልግም ፤ የጋራ ሀገርን ማልማትና ማበልፀግ ነው የምንፈልገው የሚል መልዕክት በጋራ አስተጋብተዋል” ሲሉ መናገራቸውም እነዚህ አደገኛ እሳቤዎች ሃገራዊ ሰላምና ልማት የሚያናጉ እና የህዝቦችን አብሮ መኖር አደጋ ላይ የሚጥሉ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ የዘር ፣ የመከፋፈል፣ የጎጠኝነትና የጽንፈኝነት እሳቤዎችን መጸየፍ እንደሚያስፈልግ፤ በወንድማማችነትና በአብሮነትን ላይ የተመሰረተ የጋራ ትርክት መገንባት እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ