ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት በሰላም እና ደህንነት ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ

You are currently viewing ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት በሰላም እና ደህንነት ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ

AMN-ጥቅምት 18/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት በሰላም እና ደህንነት ዙሪያ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጎልበት እንደሚሰሩ ገለጹ።

የመከላከያ ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ከሆኑት ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር ጋር በወቅታዊ የደህንነት፣ የሰላም ግንባታ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ ወቅት ሚኒስትሩ፤ ጦርነቱ በኢትዮጵያ ፍላጎት የተነሳ ባይሆንም፣ የመከላከያ ሠራዊቱ የህዝብ ደህንነትን ባከበረ መልኩ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ጥቃቱን በብቃት መመከት መቻሉን ገልጸዋል።

አክለውም በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል የባለአደራ አስተዳደር ተቋቁሞ ከስድስት ወራት በኋላ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድና ክልሉ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ሁኔታ እየተመቻቸ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በተጨማሪም መንግስት የቀድሞ ተዋጊዎችን በዲዲአር ፕሮግራም ወደ ህብረተሰቡ ለማቀላቀል እያከናወነ ላለው ተግባር የአውሮፓ ህብረት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ የልማት ፍላጎት ለማሟላት፣ ከግጭት በኋላ ማህበራዊ ተቋማትን ለማነቃቃት፣ የልማት እንቅስቃሴዎችን ለማስጀመርና ማህበረሰቡን ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ በመንግስት የሚደረጉትን ጥረቶች የአውሮፓ ህብረት እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር በበኩላቸው፤ በተደረገላቸው ገለፃ መደሰታቸውን በመግለጽ በትግራይ ክልል እየተከናወኑ ያሉ ሂደቶችን በቅርበት እየተከታተሉ መሆናቸውንና ቀደም ሲል ከነበራቸው መረጃ በላይ ግልጽ ግንዛቤ ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል።

አምባሳደሯ አክለውም፤ የአውሮፓ ህብረት ለመንግስት የሰላም እና የመልሶ ማቋቋም ጥረቶች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review