AMN- ጥቅምት 19/2019 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃዱ ተሰርዞ ለነበረው “ድምጺ ወያነ ትግራይ ሬድዮና ቴሌቪዥን አገልግሎት” ማእዶት ብሮድካስቲንግ አገልግሎት በሚል አዲስ ስያሜ የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ለብሮድካስቲንግ አገልግሎቱ በአዲስ መልክ ፈቃድ መስጠቱን አስመልክቶ የጽሑፍ መግለጫ አውጥቷል
ድምጺ ወያነ ትግራይ ሬድዮና ቴሌቪዥን አገልግሎትን አስመልክቶ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር፣ ጣቢያው ከመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ጋር የሚቃረኑ ይዘቶችን በሕገወጥ መንገድ ሲያሰራጭ በመገኘቱ ፈቃዱ መሰረዙ ይታወሳል።
ሆኖም በትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር፤ ቀደም ሲል ድምጺ ወያነ ትግራይ ሬድዮና ቴሌቪዥን በሚል የሬድዮና ቴሌቪዥን አገልግሎት ሲሰጥ የነበረዉ ጣቢያ የጦርነት መሳሪያ ሆኖ በማገልገሉ ምክንያት ፈቃዱ እንደተሰረዘ አስታውሶ፣ ይሁንና አሁን ክልሉን የሚመራው የባለአደራ አስተዳዳር የክልሉን ሰላምና መረጋጋት በማረጋገጥ እንዲሁም የሕዝብ ድምፅ በመሆን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የስያሜ ለዉጥ በማድረግ ማእዶት ብሮድካስቲንግ አገልግሎት በሚል በአዲስ ስያሜ ተቀይሮ ፈቃድ እንዲሰጠዉ ያቀረበውን ጥያቄ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ከመገናኛ ብዙሃን አዋጅ አንፃር በመመርመር ጥያቄው ተገቢነት ያለው መሆኑን በማመን ተቀብሎታል፡፡
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ማእዶት ብሮድካስቲንግ አገልግሎት በሚል አዲስ የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ የሰጠ መሆኑን ገልጾ ፣ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለብሮድካስት አገልግሎቱ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።