ኢትዮጵያና ሩሲያ ከታሪካዊ ወዳጅነት ወደ ተጠናከረ የስትራቴጂክ ወታደራዊ ትብብር

You are currently viewing ኢትዮጵያና ሩሲያ ከታሪካዊ ወዳጅነት ወደ ተጠናከረ የስትራቴጂክ ወታደራዊ ትብብር

AMN – ጥቅምት 19/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላትን ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር፣ የጦር ኃይሏን የመከላከል አቅም የሚያጠናክሩ ዘመናዊ የጦር ጀቶችን በይፋ ተረክባለች።

ይህ የጦር ጀቶች ርክክብ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ የሁለትዮሽ እና የስትራቴጂክ አጋርነት በግልጽ የሚያሳይ ሲሆን፣ የሀገሪቱን አየር ኃይል የመከላከልና የማጥቃት ብቃት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው።

የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ወታደራዊ ትብብር የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለውና በፈተናዎች ውስጥ ያለፈ ነው።

የአሁኑ ርክክብ ሁለቱ ሀገራት በዲፕሎማሲ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በወታደራዊ መስክ የገነቡት ስትራቴጂካዊ ትስስር ምን ያህል አስተማማኝና የጠነከረ ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል።

ርክክቡን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ጠንካራና ዘመናዊ የጦር ኃይል መገንባት የጦርነት ናፋቂነት ሳይሆን፣ ጦርነትን አስቀድሞ የማስቀረትና በእንጭጩ የመቅጨት ስትራቴጂ ነው።

አየር ኃይል በዘመናዊ የጦር ጀቶች መበልጸጉ ማናቸውንም ሀገራዊ ስጋቶችና ጥቃቶች አስቀድሞ በመግታት የወታደራዊ የበላይነትን በማጎናጸፍ ሰላምን የማስከበር አቅምን ከፍ ያደርጋል።

በተጨማሪም ማንኛውም የሀገርን ሉዓላዊነት እና የህዝብን ሰላም የሚፈታተን እንቅስቃሴ፣ ገና ሳይስፋፋ እና ወደ አጥፊ ጦርነት ሳይለወጥ በከፍተኛ ፍጥነትና ጥራት በቁጥጥር ሥር ለማዋል ያስችላል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል መጠናከር የሀገሪቱን ደህንነት ከመጠበቅ ባሻገር፣ ለአፍሪካ ቀንድ እና ለቀጣናው መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

የኢትዮጵያ ጸንቶ መቆም ለቀጣናው ሰላም እና ዘላቂ ልማት ዋና መሠረት ነው።

ይህ ታሪካዊ እርምጃ የሀገሪቱን ሰማይ አስተማማኝ የሚያደርግ፣ የህዝብን አደራ የሚጠብቅ እና የሀገርን ገጽታ ከፍ የሚያደርግ ኩራት ነው።

እንዲሁም የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም፣ የድንበር ሉዓላዊነት እና የቀጣናውን መረጋጋት ለማረጋገጥ የተወሰደ ታላቅ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review