አዲስ አበባ፤ የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ማዕከልነቷን አጠናክራ ቀጥላለች

You are currently viewing አዲስ አበባ፤ የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ማዕከልነቷን አጠናክራ ቀጥላለች

AMN- ጥቅምት 21/2019 ዓ.ም

አዲስ አበባ፤ የበርካታ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መሥራችና ዋና መቀመጫ በመሆን አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሚናዋን በላቀ ሁኔታ እያስቀጠለች ትገኛለች።

ከተማዋ ከኒውዮርክ እና ከጄኔቫ ቀጥሎ እጅግ በርካታ የውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች እና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች የሚገኙባት ሦስተኛዋ የዓለም ከተማ መሆኗ ይታወቃል።

ከ120 በላይ የሚሆኑ የውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች፣ ከፍተኛ ሚሲዮኖች እና ቋሚ ልዑካን ቡድኖችም በከተማዋ ይገኛሉ።

ይህ እውነታ አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ፖለቲካዊ እና የዲፕሎማሲ ደረጃዋን ከፍ እንደሚያደርገው የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በተለይም አፍሪካዊ ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሔ እንዲያገኙ የሚደረጉ የሰላም ውይይቶች፣ ድርድሮች እና የዲፕሎማሲ ጥረቶች ማዕከል በመሆን የምትጫወተው ሚና እጅግ የጎላ ነው።

በየዓመቱ የሚካሄደውን የአፍሪካ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንን የመሪዎች ጉባኤን ጨምሮ፣ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ የሀገራት መሪዎችና ዲፕሎማቶች ስትራቴጂካዊ ውይይቶችን የሚያደርጉባት ዋና ማዕከልም ናት።

የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአንድ ወቅት እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ከተማዋን የብልጽግና ምልክት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል እያደረጋት ይገኛል።

ከተማ አስተዳደሩም ከተማዋ ከዓለም መሪ የዲፕሎማሲ ማዕከላት መካከል አንዷ እንድትሆን በማድረግ፣ ለዓለም አቀፍ ጉባኤዎች እና ለገጽታ ግንባታ ጥረቶች ያላት ሚና እንዲጠናከር አድርጓል።

በቅርብ ዓመታት በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉት የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች እና አረንጓዴ ስፍራዎች ከተማዋን ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎች እንዲሁም ለዲፕሎማቶች እና ለቱሪስቶች ይበልጥ ተስማሚ፣ ሳቢና ዓለም አቀፍ ደረጃዋን የጠበቀች እንድትሆን አስችሏታል።

የዲፕሎማሲ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ፤ የጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ተምሳሌትነቷን አስጠብቃ የሰላም፣ የዕድገት እና የትብብር ማዕከል ሆና አሁንም ቀጥላለች።

ይህ ታሪካዊና ወቅታዊ ቁመናዋም አዲስ አበባ የአፍሪካ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ዋና ማማ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላት ሆና እንድትቀጥል አስችሏታል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review