ኢትዮጵያ ተሞክሮዋን ከማካፈል አልፋ ኮፕ32 ጉባኤን ለማስተናገድ የሚያስችሏትን ልምዶች እየቀመረች ነዉ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ተሞክሮዋን ከማካፈል አልፋ ኮፕ32 ጉባኤን ለማስተናገድ የሚያስችሏትን ልምዶች እየቀመረች ነዉ

AMN- ኅዳር 7/2019 ዓ.ም

በቱርክ አንታልያ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው 31ኛው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP 31) የመጀመሪያ ሳምንቱን አጠናቆ ዛሬ ሁለተኛ ሳምንቱን ጀምሯል።

ጉባኤው በመጀመሪያው ሳምንት ቆይታው በተለያዩ አበይት ጉዳዮች ላይ የመሪዎች እና የባለሙያዎች ምክክሮችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

በመጀመሪያው ሳምንት ማጠቃለያ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የፋይናንስ ስርዓቱ መሰረታዊ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።

በተለይም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ጉዳት ለሚያስተናግዱ ታዳጊ ሀገራት ተገቢው የገንዘብ ድጋፍና ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ ጠንካራ መልእክት አስተላልፈዋል።

እንዲሁም ነዳጅ አምራች ሀገራት እና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ከባቢ አየርን ከሚበክሉ የኃይል አማራጮች የመላቀቅ ፍጥነት እና አቅጣጫን በተመለከተ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።

የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሳይመን ስቲል በበኩላቸው፣ ተደራዳሪዎች በሁለተኛው ሳምንት በዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ፈጣን እና አጥጋቢ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ አቅርበዋል።

በመጀመሪያው ሳምንት በጥቂት ጉዳዮች ላይ ብቻ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን፣ በርካታ ትኩረት የሚሹ አጀንዳዎች ወደ ሁለተኛው ሳምንት ተሸጋግረዋል።

ጉባዔው በዚህ ሳምንት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ታዳጊ ሀገራት ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ የሚደረግበት እና ጉዳቱን ለመቋቋም የሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ በስፋት ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የደረሰውን ጉዳት ለመቋቋም በሚያስችሉ አሰራሮች ዙሪያ ከአደጉ ሀገራት እና ተቋማት ጋር ሰፊ ምክክሮችም ይደረጋሉ።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ መጪውን የኮፕ ጉባኤ ለማስተናገድ የሚያስችሏትን ቅድመ ዝግጅቶች እና እየሰራቻቸው ያሉ ስራዎችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ ላይ ትገኛለች።

ለአደጉ ሀገራት ጭምር ተምሳሌት የሚሆኑ አረንጓዴ ልማት ተግባራቶቿን በዚህ ሳምንትም አጠናክራ በመቀጠል፣ ሀገራዊ ወዳጅነትን የማስተሳሰር ስራዎቿን አጠናክራ እንደምትቀጥል ይጠበቃል፡፡

የአንታልያው የCOP 31 ጉባኤ በቀጣዮቹ ቀናት የቀሩትን አበይት አጀንዳዎች በመፈተሽ እና ተስማሚ መፍትሄዎችን በማመላከት ፍጻሜውን ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review