AMN- ኅዳር 2/2019 ዓ.ም
ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ፋይናንስ አቅርቦትን በማሳደግ ታዳጊ ሀገራትን መደገፍ እንደሚገባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ።
ዋና ፀሐፊው ታዳጊ ሀገራት ወደ ንጹህ ኃይል የሚያደርጉትን ሽግግር እንዲያፋጥኑም ጥሪ አቅርበዋል።
በቱርኪዬ አንታሊያ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው 31ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ «ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት በተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን» በሚል መሪ ቃል በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ የበለጸጉ እና ከፍተኛ በካይ ጋዝ የሚያመነጩ ሀገራት ያደረሱትን ጉዳት ተመጣጣኝ ካሳ በመክፈል፣ ለታዳጊ ሀገራት የሚውል 1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ዶላር የአየር ንብረት ፋይናንስ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም የዓለም አቀፍ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን በየዓመቱ በስድስት በመቶ መቀነስ እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአየር ንብረት ቀውሱ እየቀደመን ነው ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊከሰት የሚችለውን አስከፊ አደጋ ለመግታት የሚያደርገው እንቅስቃሴ እጅግ አዝጋሚ መሆኑን አመልክተዋል።
አሁን ያሉት ብሔራዊ የአየር ንብረት ቃልኪዳኖች ሙሉ በሙሉ ቢተገበሩ እንኳ በዓመት ከሚያስፈልገው የልቀት ቅነሳ መጠን ማሳካት የሚችሉት አንድ ሦስተኛውን ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሁን ያለው አካሄድ ከቀጠለ እስከ ክፍለ ዘመኑ መጨረሻ የዓለም ሙቀት ከ2 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንደሚጨምር ያስጠነቀቁት አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ ይህም ሊመለሱ የማይችሉና አስከፊ የተፈጥሮ ቀውሶችን እንደሚያስከትል አሳስበዋል።
በመሆኑም ዓለም ወደ ታዳሽ ኃይል የሚደረገውን ሽግግር ማፋጠን፣ ተጋላጭ ማህበረሰቦችን ከአየር ንብረት አደጋዎች የመጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት እንዲሁም መንግሥታት ከቃልኪዳን አልፈው በተግባር የተደገፉ እርምጃዎችን እንዲወስዱ አሳስበዋል።
ዋና ፀሐፊው አያይዘውም፤ በካይ ጋዝ የሚለቁ በለጸጉ ሀገራት ለአየር ንብረት ቀውሱ ተገቢውን ኃላፊነት እንዲወስዱ፣ የታዳጊ ሀገራትን አቅም የሚያጠናክር የፋይናንስ ድጋፍ እንዲጨምሩ እና በካዮች ተገቢውን ካሳ መክፈል አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።
ከዚህም ባለፈ መንግሥታት በነዳጅ ኩባንያዎች ከፍተኛ ትርፍ ላይ ታክስ በመጣል በአየር ንብረት ጉዳት ለደረሰባቸው ሀገራት ድጋፍ እንዲውል አድርገዋል።
ታዳጊ ሀገራት ያለተጨማሪ የኢኮኖሚ ጫና ወደ ንጹህ ኃይል መሸጋገር እንዲችሉ፤ ተመጣጣኝ የፋይናንስ አቅርቦት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ጠንካራ የዝግጁነት እርምጃዎች እና የተቀናጀ ዓለም አቀፍ ትብብርን ያካተተ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።