ኢትዮጵያ ለ5ኛው የአፍሪካ የማኅበረሰብ ጤና ጉባኤ በቂ ዝግጅት አድርጋለች

You are currently viewing ኢትዮጵያ ለ5ኛው የአፍሪካ የማኅበረሰብ ጤና ጉባኤ በቂ ዝግጅት አድርጋለች

AMN – ጥቅምት 23/2019 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ለሚካሄደው 5ኛው የአፍሪካ የማኅበረሰብ ጤና ጉባኤ በቂ ዝግጅት መደረጉን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጂያን ካሲያ ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ጉባኤውን ለማዘጋጀት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጓን ገልፀዋል።

ከኅዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ በጤና ሚኒስቴር እና በአፍሪካ ሲዲሲ ትብብር መዘጋጀቱን ዶ/ር መቅደስ አስረድተዋል።

ጉባኤው ቀጣናዊ የጤና ትብብርን እንደሚያጠናክር የገለጹት ሚኒስትሯ፣ የጋራ የጤና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እንደሚያስችልም አብራርተዋል።

ጉባኤው የጤና ስርአታችንን ለሌሎች የምናሳይበት እና ከሌሎች ሀገራትም የልምድ ልውውጥ የምናደርግበት ነው ያሉት ዶ/ር መቅደስ፣ የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ፣ የጤና ዲጂታይዜሽን እና የጤና ቱሪዝምን ለማስፋፋት የአፍሪካ ሀገራት የሚመክሩበት ነው ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጂያን ካሲያ በበኩላቸው፣ ለኢትዮጵያ መንግሥት፣ ለጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ለጉባኤው ድጋፍ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በጉባኤው የጤና አውደ ርዕይ እንደሚቀርብ ያስረዱት ዶ/ር ጂያን፣ መድረኩ የአፍሪካ የጤና ዘርፍ የደረሰበትን ደረጃ ማሳያ እንደሚሆን አክለዋል።

በጉባኤው ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ከ1 ሺህ በላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review