AMN- የካቲት 8/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በዓለም ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን በተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት ፕሬዚዳንት ጄፍሪ ሳክስ(ፕ/ር) ገለጹ።
ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያን ዕድገት በተጨባጭ ለመረዳት በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የታዩትን የኢኮኖሚ ለውጦች መመልከት በቂ መሆኑን ጠቁመዋል።
በየዓመቱ በአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ በሚመጡበት ወቅት በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ የልማትና የዕድገት ለውጦችን መታዘባቸውንም ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ግንባታ፣ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች፣ የመንገድ መሠረተ ልማት መስፋፋት፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን የመሳብ ዐቅም መጨመርን በአብነት አንስተዋል።
ለዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ አስተዋፅኦ ማበረከቱን ነው የተናገሩት።
አክለውም ኢትዮጵያ የዛሬን ብቻ ሳይሆን የመጪውን ጊዜ አርቃ በማሰብና በማለም የምትተጋ ታላቅ ሀገር መሆኗን በተግባር አረጋግጣለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የፀሐይ፣ የንፋስና የጂኦተርማል ኃይል እምቅ ዐቅም እንዳላት በማንሳት፤ ይህንንም እየተጠቀመች መሆኑን አመላክተዋል።
በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን በአካል መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ይህም የአርሶ አደሩን ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ የኑሮ ደረጃውን እያሻሻለ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
አርሶ አደሩ በሜካናይዜሽንና በኤሌክትሪክ ተደራሽነት ሲታገዝ ምርታማነቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምርም ጠቁመዋል።
በግብርናው ዘርፍ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለው ውጤት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም በስንዴ ልማት የተመዘገበው ስኬት ሀገሪቱ ራሷን ከመቻል አልፋ ለሌሎችም መትረፍ እንደምትችል ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
አኅጉራዊ የንግድ ልውውጥን እና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ሀገራት በመንገድ፣ በባቡር እና በኃይል ማመንጫ የልማት ሥራዎች ተሣሥረው መሥራት እንዳለባቸውም ምክረ ሐሳባቸውን መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።