AMN- ሚያዝያ 6/2018 ዓ.ም
የቤት አቅርቦትን ለማሳደግ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል። ከንቲባዋ የትም ሀገር መንግስት ለዜጎች ቤት እየገነባ ሊያቀርብ አይችልም ያሉ ሲሆን፣ ስለ ቤት አቅርቦት ስንናገር በመሠረታዊነት የግንዛቤ ማስተካከያ እንደሚያስፈልግና ይህም አማራጭ የቤት አቅርቦትን መጨመር ነው ሲሉ አንስተዋል፡፡
በዚህም መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ 600 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ግብ አስቀምጦ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ለዚህ ስኬትም አራት ዋና ዋና የቤት ልማት ማዕቀፎች መለየታቸውን የገለጹት ከንቲባዋ፣ መንግስት በበጀት የሚገነባቸው ቤቶች፣ በግሉ ሴክተርና በመንግስት ትብብር የሚገነቡ፣ ዜጎች በማህበር ተደራጅተው የሚገነቧቸው እና በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚገነቡ ቤቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የመቶ ሺህ ቤቶች ግንባታ መጀመሩን በመግለጽም፣ ግንባታውን ይበልጥ ለማቀላጠፍም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት፣ የቤት አቅርቦቱን በገንዘብ ለመደገፍ የሚያስችል የቤት መግዣ ብድር (የሞርጌጅ) ባንክ እንዲቋቋም በሚገባ እየተሠራበት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
አዲስ አበባም የዚህ ተጠቃሚ በመሆን የአንበሳውን ድርሻ እንደምትወስድ ነው የገለጹት።
በታምራት ቢሻው