AMN- ሚያዚያ 6/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአምራች ከኢቢሲ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሀገርን ሉዓላዊነት ከማረጋገጥ ጀምሮ እስከ ዘመናዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ያለውን የማይተካ ሚና በዝርዝር አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ማኑፋክቸሪንግ ለኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን አንድ ሀገር ራሷን ችላ በሉዓላዊነት ለመቆም መሰረታዊ ፍላጎቶቿን በራሷ አቅም ለሟሟላት እንደሚያስችላት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢንዱስትሪ ለዘመናት የቆዩ አሰራሮችን በመቀየር ረገድ ያለውን ፋይዳ ሲገልጹ፣ በምሳሌነት ግብርናን ጠቅሰዋል።
ለሺህ ዓመታት በበሬ ሲታረስ የቆየው የግብርና ስርዓት ለውጥ ማምጣት የቻለው የኢንዱስትሪ ውጤቶችና ቴክኖሎጂዎች ሲገቡበት መሆኑን አስታውሰዋል።
ማኑፋክቸሪንግ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ዘርፎችም የፈጠራና የቴክኖሎጂ ምንጭ በመሆን እድገትን እንደሚያፋጥን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ማኑፋክቸሪንግ ከኢኮኖሚ በዘለለ ከሀገር ክብርና ነጻነት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያሉ ሲሆን ይህም፤ የራሱን ምግብ፣ ልብስና መድኃኒት በበቂ ሁኔታ የማያመርት ሀገር የዜጎቹን ደህንነት ለመጠበቅና እንደ ሀገር ለመቆም ይቸገራል።

ዘርፉ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከሌሎች ሴክተሮች በላቀ ሁኔታ ውጤታማ መሆኑን እና የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን ባለፈ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት ቁልፍ መሳሪያ ነው ብለዋል።
መንግስት ትኩረት ከሰጣቸው አምስት ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል አንዱ ኢንዱስትሪ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ዐቢይ፣ ዘርፉ ኢኮኖሚውን ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ለማሸጋገር እንደ ማስፈንጠሪያ እንደሚያገለግል አስረድተዋል።
አክለውም ኢንዱስትሪን በበቂ ደረጃ ካልመራንና ካላሳካን የምናስበውን ብልፅግና ለማምጣት ያስቸግራል በማለት፣ ዘርፉ ለሀገራዊ ግስጋሴ ያለውን ከፍተኛ ድርሻ አረጋግጠዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ