AMN – ሚያዝያ 5/2018 ዓ.ም
ከመርከብ መከታተያ ወይም ማሪን ትራፊክ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ቀይ ምልክቶች የነዳጅ እና የጋዝ ጫኝ መርከቦችን ያመለክታሉ።
አረንጓዴ ምልክቶች ደግሞ እንደ እህል እና የብረት ማዕድን ያሉ ሸቀጦችን የሚጭኑ ደረቅ ጭነት መርከቦችን ያሳያሉ። የሶስት ማዕዘን ቅርጽ ያላቸው ምልክቶች የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን ሲያሳዩ፣ ክብ ምልክቶች ደግሞ የቆሙ ወይም መልሕቅ የጣሉ መርከቦችን ያመለክታሉ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ኢራን በሚገቡና በሚወጡ መርከቦች ላይ የጣሉት እገዳ መጠናቀቁን ተከትሎ በቀጣናው ምን ሊከሰት ይችላል የሚለዉ የበርካቶች መነጋገሪ ሆኗል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ወደ እገዳው ቀጠና ለመቅረብ የሚሞክሩ ማንኛውም የኢራን “ፈጣን ተዋጊ መርከቦች” ከተገኙ “ወዲያውኑ እንደሚደመሰሱ” ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ትራምፕ በባህር ላይ ባሉ የዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ የምንጠቀመውን ዓይነት እርምጃ በኢራን ላይ ልንጠቀም እንችላለን ብለዋል፡፡
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ ፈጣን ጥቃት ሰጪ ጀልባዎች፣ አነስተኛ የባህር ሰርጓጅ መርከቦች፣ ፈንጂዎች እና በፍንዳታ የተሞሉ ጄት ስኪዎችን ጨምሮ በርካታ አማራጮች እንዳሉት ቀደም ብሎ በመግለጽ ላይ ይገኛል፡፡

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተኩስ አቁሙን የሚያናጋ ወይም ግጭቱን የሚያባብስ ማንኛውንም ድርጊት በማያሻማ ሁኔታ እንዲቆም አሳስበዋል።
ዋንግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ዳግም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ መከላከል እና በከባድ ትግል የተገኘውን የተኩስ አቁም ሂደት ማስቀጠል ነው ብለዋል።
ፓኪስታን ግጭቱን በንግግር ለመፍታት ያደረገችውን ጥረት ያደነቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቤጂንግም የድርሻዋን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ማናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ኢራን በሚገቡና በሚወጡ መርከቦች ላይ የጣሉት እገዳ መጠናቀቁን ተከትሎ በአካባቢው በሚገኙ መርከቦች ላይ የፍተሻ ሂደቶች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ ማምሻውን የወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ