አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ እገዳ እንደምትጥል አስታወቀች

You are currently viewing አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ እገዳ እንደምትጥል አስታወቀች

AMN- ሚያዝያ 5/2018 ዓ.ም

ዓለም በጉጉት ሲጠብቀዉ የነበረዉና በኢስላማባድ የተካሄደዉ የአሜሪካ እና የኢራን የተኩስ አቁም ንግግር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በአንድ በርሜል ከ100 ዶላር በላይ እየተሸጠ ይገኛል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ንግግሩ ያልተሳካው ኢራን የኒውክሌር ምኞቷን ለመተው ፈቃደኛ ስላልሆነች ነው ሲሉ፣ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸዉ አሜሪካ የንግግሩን ሕግ በመቀያየሯ ነዉ ሲሉ ከሰዋል።

ይህንን ተከትሎ የአሜሪካ ጦር ከሰኞ ጀምሮ ወደ ኢራን ወደቦች እና የባህር ዳርቻዎች የሚገቡትንም ሆነ የሚወጡትን ማንኛውንም የባህር ላይ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያግድ አስታዉቋል፡፡

ወደ ሌሎች አገሮች የሚሄዱ ወይም ከሌሎች አገሮች የሚመጡና በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ግን ጉዞአቸዉን አያደናቅፍም፡፡

ይህ የአሜሪካ ዉሳኔ ለሁለት ሳምንታት ያህል የቆየውን የተኩስ አቁም ስምምነት አደጋ ላይ ይጥለዋል ተብሎ ተሰግቷል፡፡

የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰኞ ጀምሮ አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ እገዳ እንደምትጥል ነዉ ያስታወቁት፡፡

የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሃገራቸው በዛቻ እንደማትሸነፍ የገለጹ ሲሆን፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ ወደ ባህር ወሽመጡ የሚጠጉ ወታደራዊ መርከቦች ከባድ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ሲል አስጠንቅቋል፡፡

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ብሪታንያ እገዳውን አትደግፍም፤ ይልቁንም ትኩረቷ የባህር ወሽመጡ ክፍት እንዲሆን እና የነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ ማድረግ ላይ ነዉ፡፡

በርካታ የዓለም ሃገራት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ወደቦች ላይ የጣሉትን እገዳ በመቃወም ላይ ናቸው።

የስፔን መከላከያ ሚኒስትር ማርጋሪታ ሮብለስ እስካሁን ከተሰሙት ጠንከር ያሉ ንግግሮችን በመጠቀም፣ የቀረበው ሀሳብ ምንም ትርጉም የሌለው ነው ብለዋል።

ቻይና ሁሉም ወገኖች እንዲረጋጉ ያሳሰበች ሲሆን፣ የሆርሙዝ ሰርጥን ክፍት ማድረግ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጋራ ፍላጎት መሆኑን ገልጻለች።

በደቡብ ምስራቅ እስያ የሚገኙ 11 አገራት ስብስብ የሆነው አሴአን፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር፣ የባህር ላይ ደህንነት እና የአሰሳ ነፃነት እንዲረጋገጥ ጥሪ አቅርቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ማክሮን፣ ፈረንሳይ እና ብሪታንያ በመጪዎቹ ቀናት በባህር ወሽመጡ ያለውን የነፃ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያስችል ጉባኤ እንደሚያዘጋጁ ማስታወቃቸዉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

አሁን በወጡ መረጃዎች የኢራን የባህር ኃይል ለአሜሪካ የጦር መርከብ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በኢንተርኔት መሰራጨቱን ተከትሎ በቴህራን እና በዋሽንግተን መካከል ያለው ውጥረት ይበልጥ ተባብሶ መቀጠሉም ተዘግቧል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review