AMN- ሚያዚያ 6/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ሲተገበሩ የነበሩ አንዳንድ የኢንቨስትመንት አቅጣጫዎች ለሀገሪቱ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትና የዕዳ ጫና ምክንያት መሆናቸውን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአምራች ኢንደስትሪ ዘርፍ እንቅስቃሴ ዙሪያ በሰጡት ቃለ ምልልስ ፣ በከፍተኛ ትምህርት፣ በስፖርት መሠረተ ልማት እና በጤናው ዘርፍ የታዩ የሀብት ብክነቶችን በዝርዝር አብራርተዋል።
ዩኒቨርሲቲዎችን እንደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በየዞኑ መበተን የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ካለማጥናት የመጣ ስህተት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ሊይዙ የሚችሉ ባዶ ሕንፃዎች መኖራቸውን ጠቁመው ትኩረት መደረግ የነበረበት በታችኛው የትምህርት እርከን ላይ እንደነበር አስረድተዋል።
መንግሥት ይህንን ስህተት ለማረም ባለፉት ስድስት እና ሰባት ዓመታት ውስጥ ከ34 ሺህ በላይ መዋለ ሕፃናትን በመገንባት የታችኛውን የትምህርት እርከን ለማጠናከር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ነው የጠቀሱት።
ቀደም ሲል በመንግሥት ደረጃ አሥር መዋለ ሕፃናት እንኳ እንዳልነበሩ በማስታወስ ፣ የአንድ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ወጪ እጅግ በርካታ መዋለ ሕፃናትን መገንባት እንደሚችልና ይህም ለሀገር ግንባታ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አብራርተዋል።
በአንድ ከተማ ውስጥ በዩኒቨርስቲዎችና በከተማ አስተዳደሮች በአጭር ርቀት ላይ ስታዲየሞችን መገንባት አደገኛ በሽታ ሆኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ እነዚህ ስታዲየሞች አንዳቸው የካፍ መስፈርትን አለሟሟላታቸውን አስረድተዋል።
ሐብትን ሰብሰብ አድረጎ ማዋል ቢቻል ኖሮ ደረጃውን የጠበቀ አንድ ስታዲየም መገንባት ይችሉ እንደነበር ነው የጠቀሱት።
በጤናው ዘርፍም በተለያዩ ከተሞች የተገነቡ ሆስፒታሎች በቂ የሕክምና መሣሪያዎች ሳይሟሉላቸው እንደ ሕንፃ ብቻ ቆመው መቅረታቸውን ለብክነት ማሳያ አድርገው አቅርበዋል።
የሆስፒታሎቹን የአልጋ ቁጥር በመመጠን የሕክምና ቁሳቁስ ማሟላት ላይ መተኮር እንደነበረበት ነው የገለጹት፡፡
የከተሜነትን አስፈላጊነት በተመለከተ ባነሱት ሐሳብ ፣ ጥግግት ያለው የከተማ ማኅበረሰብ ለኢኖቬሽን፣ ለውድድር እና ለግብር አሰባሰብ ምቹ መሆኑን ጠቁመው የተበተነ ማኅበረሰብ ለልማት እና ለሀገር ግንባታ ፈታኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የልማት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ መንግሥታቸው ቀደምት መንግሥታት የጀመሯቸውን ጠቃሚ ፕሮጀክቶች የቀድሞ ናቸው ሳይል እያጠናቀቀና እያዘመነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በታደሠ ሽፈራው