የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ለጤናው ዘርፍ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ተጠቁሟል
ወጣት ቤተልሔም አለነህ ትባላለች፡፡ ራስ መኮንን ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወልዳ አድጋለች። የመጀመሪያ ትምህርቷን የተማረችው በዳግማዊ ምኒሊክ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምርቷን በዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከመኖሪያ ቤቷ ወደ ትምህርት ቤት ስትሄድ ከወንዙ በሚወጣው ሽታ ምክንያት ሳይነስ ትታመም እንደነበር ታስታውሳለች፡፡
“ከዚህ ቀደም በየጥጋጥጉና በየወንዝ ዳርቻዎች የሚጣሉ ቆሻሻዎች አይደለም ለመዝናናት ይቅርና የግድ ካልሆነ በዚያ በኩል ለማለፍም አይጋብዙም። አማራጭ መንገዶችን ለመጠቀም የሚያስገድድ ሁኔታ ነበር” የምትለው ወጣት ቤተልሔም፤ አሁን ላይ በእግር መጓዝን ልምድ አድርጋለች፡፡ ወደ ስራ የምታደርገውን የመኪና ጉዞ ወደ እግር መንገድ ቀይራለች፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የተከናወነው ልማት የሚታይ፣ የሚዳሰስና መዓዛው የሚስብ ነው። የተፈጥሮን ውበት ለማድነቅ፣ እድሜ እየጨመረ ሲመጣ ለስኳርና ለደም ግፊት በሽታ የመጋለጥ ሁኔታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል፣ ጥሩ ሐሳቦችን ለማውጠንጠን የእግር ጉዞ ማዘውተር እንደሚያስፈልጋት ተረድታለች፤ ይህንንም መከወን ጀምራለች፡፡
“የወንዞች መበከል የእግር ጉዟችን ላይ ቀጥተኛ የሆነ ተፅእኖ አለው፡፡ አሁን ግን ወንዞቻችን መታከም መቻላቸው የእግር ጉዞ እንድናዘወትር አግዞናል። ቢደክመን እንኳን አረፍ የማለት እድልን አግኝተናል” የሚሉት ደግሞ አቶ ሰለሞን መላኩ ናቸው፡፡ ወደ ፒያሳ በቀን ሁለት ጊዜ ይመላለሳሉ፡፡ ጠዋት ወደ ስራ ማታ ደግሞ ከስራ ወደ ቤት ለመግባት ሲሉ የታክሲ አገልግሎት ለመጠቀም ፒያሳን ይረግጣሉ፡፡ አልፎ አልፎ ቅዳሜ እና እሁድ ከጓደኞቻቸው ጋር ሻይ ቡና ለማለት ምርጫቸው ይኸው ሰፈር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
አቶ ሰለሞን ፒያሳ የነበራትን ያረጁ ቤቶችና፣ አሮጌ ቆርቆሮዎች እንዲሁም የተበከሉ ወንዞቿን ጠንቅቀው ያውቋቸዋል፡፡ የውስጥ ለውስጥ መንገዶቿ የቆሸሹ፣ ከቤት እና ከተቋማት የሚወጡ ፍሳሽ ቆሻሻዎች ከቱቦዎች ጋር እየተሰባሰቡ ወደ ወንዞች የሚቀላቀሉበት ሁኔታ በመኖሩ ምክንያት በጠራራ ፀሐይ በመሃል ፒያሳ ከታለፈ ጉንፋንን ጨምሮ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ ያደርጋል፡፡ በዚያን ወቅት በወንዞች አካባቢ ሲያልፉ ይሸታቸው የነበረው ሽታ አለርጂካቸውን ይቀሰቅስባቸው ስለነበር፤ አፍንጫቸው የመታፈንና ቶሎ ቶሎ የማስነጠስ ሁናቴ ሲገጥማቸው መቆየቱን አልሸሸጉም። አሁን ግን በታከመው አካባቢ አየር የመቀበል፣ በወንዝ ዳርቻዎች አካባቢ በተሰናዱ ወንበሮች ላይ ጥሩ ቆይታ የማድረግ ልምድ እንዳላቸው ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
አባ ብርሃኑ አንዱዓለም ከጥቂት ዓመታት በፊት፤ “ዶሮ ማነቂያ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ኖረዋል። ከልማቱ በፊት አዲስ አበባን የሚያውቋት ከስሟ በተቃራኒው መንገድ ነበር። ክረምት ሲገባ ወንዞች ከየአካባቢው የሚለቀቁ ቆሻሻዎችን ተሸክመው እንዲጓዙ የተፈረደባቸው ይመስል ነበር፡፡ ይህም ለነዋሪው የጤና ጉዳት ሲያስከትል መቆየቱን ተናግረዋል።
“ከተማችን እንደ አደጉት ሀገራት መንገዶቿ ምቹ ከመሆናቸው ባሻገር ወንዞቻችን የሚጎበኙ ስፍራዎች ሆነው እንደማየት አስደሳች ነገር የለም” የሚሉት አባ ብርሃኑ፤ ወንዞቻችን አሁን ላይ የበሽታ ምንጭ ብሎም ስጋት ሳይሆኑ፤ የአይንና የቀልብ ማረፊያ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከመላው ኢትዮጵያ ከተወጣጡ የጤና ባለሙያዎች ጋር ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም ውይይት ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የተሠሩ የልማት ሥራዎች በቃል የተነገረውን የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ ያደረጉ ናቸው፡፡ በወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት አስደናቂ ሥራ እየተሰራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በፕሮጀክቱ ለበሽታ ምክንያት የነበረን አካባቢ ወደ ጤናማ ስፍራ የመቀየር ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ “ንጹህ አካባቢ እንፍጠር፤ ሰው በአካል ብቃት ንቁ ይሁን” ማለት ቀጥታ ከመከላከል ጋር የሚያያዝ ሥራ ስለመሆኑ አንስተው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የጤና ማበልጸግ እና በሽታ መከላከል ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ቢሳ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስረዱት፤ የጤና ፖሊሲያችን እንደሚደግፈው ዜጎች ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው፡፡ ንፅህናው በተጠበቀ አካባቢ ላይ መኖር ተላላፊ እና ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ለመጠበቅ ያስችላል፡፡ በሽታን ቀድሞ መከላከልና አክሞ የማዳን አቅምን ከፍ ለማድረግ ያስችል ዘንድ የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራ ቀላል የማይባል አበርክቶ አለው፡፡ የታከሙ ወንዞች ጤናማ ማህበረሰብን በመፍጠር ረገድ አይተኬ ሚና አላቸው፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ አንድ ሰው ጤናማ በሆነ አካባቢ መኖር ሲችል በርካታ የጤና በረከቶችን እንዲያገኝ ያግዘዋል፡፡ የጤና ፖሊሲያችንም ይህንን ማዕከል አድርጎ የአካባቢ ንፅህናን በተመለከተ የደረቅ እና የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓታችን የህብረተሰቡን ጤና በማይጎዳ መንገድ እንዲሆን ደንግጓል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሰዎች በቀላሉ ተላላፊ ብሎም ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ከማድረግ አንፃር ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ በሽታ የሚተላለፍባቸው ሶስት ዋና ዋና መንገዶች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ጌቱ በአየር፣ በውሃ እንዲሁም በአፈር ብክለት አማካኝነት የበሽታ መተላለፊያ መንገዶቹ እንደሚጨምሩ አስታውቀዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወንዞቻችን ታክመው ለማየት በመቻላችን የማህበረሰብ ጤና ከመጠበቅ አልፎ ወንዞች አካባቢ ጥሩ የጥሞና ጊዜ ለማሳለፍ የሚቻልበት አግባብ ስለመፈጠሩ አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ ጌቱ ገለፃ፤ ከዚህ ቀደም በየወንዙ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች በግዴለሽነት ይጣላሉ፡፡ ሰዎች ካለምንም እፍረት ይፀዳዳሉ፤ እንዲሁም ሆቴሎች ብሎም ግለሰቦች የሽንት ቤት ፍሳሾችን ከወንዞች ጋር ያገናኛሉ፡፡ ይህ ማህበረሰቡ ለመተንፈሻ አካላት ችግር የመጋለጥ እድሉ ሰፊ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በተለይም ለአለርጂ፣ ለአስም፣ ለሳንባ ነቀርሳ እና ለመሳሰሉት በአየርና በአፈር ብክለት አማካኝነት ለሚነሱ በሽታዎች ተጋላጭ የሚሆንባቸው እድል እጅግ ሰፊ ነበር፡፡ የወንዝ ዳርቻ ልማት ለጤና አገልግሎት ዘርፍ ትልቅ አበርክቶ አለው፡፡
በተጨማሪም አሁን ላይ በወንዝ ዳርቻዎች አካባቢ ያሉ መንገዶች ለእግረኞች ምቹ ሆነዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሰዎች የእግር ጉዞ እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በወንዝ ዳርቻ አካባቢዎች አይደለም የእግር መንገድ ጉዞ ማድረግ ይቅርና ቦታው ላይ ሲደረስ አፍና አፍንጫን በመያዝ ፈጠን ባለ እርምጃ ለማለፍ ነበር ሰዎች የሚሯሯጡት፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ እንደ ጉንፋን ላሉ በሽታዎች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ስጋት ስለሚያድርባቸው ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሰዎች በተበከሉ ወንዞች አካባቢ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚገደቡበት አግባብ ሰፊ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያትም እንደ ደም ግፊትና ስኳር ያሉ በሽታዎችን ለመከላከል ጥረት የማድረግ ሁኔታ የተቀዛቀዘ እንዲሆን ያደርግ ነበር፡፡ አሁን ግን ሰዎች ጤናማ እንቅስቃሴ ለማድረግ አመቺ ሁኔታዎች ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል፡፡
ህክምና ቦታ ሄዶ መድኃኒት በመውሰድ ብቻ መፍትሄ ማምጣት አይቻልም የሚሉት አቶ ጌቱ፣ ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው አካባቢን በተቻለ መንገድ ንፁህ ማድረግ ነው፡፡ የሰው ልጅ ጤና መታከም የሚጀምረው አካባቢው ላይ ከሚያየው መልካም የተፈጥሮ ገፀ በረከት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ብዙ ጊዜ በውሃ ብክለት ሳቢያ ለሚከሰት የውሃ ወለድ በሽታ ሰዎች የመጠቃት እድላቸው ሰፊ የሚሆነው በተለይ በወንዝ ዳርቻዎች ላይ ቆሻሻዎች አለአግባብ ሲጣሉ ነው፡፡ በመሆኑም አካባቢው ላይ የሚኖሩ ሰዎችን በቀላሉ ለውሃ ወለድ በሽታ ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ አሁን ላይ ግን ከወንዞቹ የሚለቀቀው ፈሳሽ ውሃ ፍፁም ጤናማ እና የሰዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የማይረብሽ ነው፡፡
አቶ ጌቱ በማብራሪያቸው፣ የወንዞች ንፅህና ተጠብቆ ይቆይ ዘንድ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በመንገድ ዳር የተሰሩ መጸዳጃ ቤቶች በምን ያህል ርቀት መሰራት አለባቸው፣ የመፀዳጃ ቤቶቹ ውሃ አላቸው ወይ፣ በአግባቡ ይያዛሉ ወይ የሚለውን ቴክኒካል ድጋፎችን ከማድረግ ባሻገር ቢሮው የጤና ትምህርት ጭምር እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በመልዕክታቸው እንደጠቆሙት፤ ወንዞችን የማልማት ሥራን በሁሉም አካባቢዎች ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ ይህ የሚደረገው የህብረተሰቡ ጤና እንዲጠበቅ ከማሰብ አንፃር ነው፡፡ የቀሩ የቤት ሥራዎችን ለመስራት ደግሞ የሁሉም ኃላፊነት ነው። ወንዞች እንዳይበከሉ ግለሰቦች ብሎም ድርጅቶች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በሽታን አስቀድሞ መከላከል ላይ በሚሰራው ሥራ የወንዝ ዳርቻዎችን ማልማት ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም፡፡
በሄለን ጥላሁን