AMN – ሚያዚያ 11 / 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከጀመረ ወዲህ ፣ በአምራች ኢንደስትሪው ስርነቀል ለውጥ እያመጡ ያሉ ስኬቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ሀገሪቱ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ለምታደርገው ሽግግር ትልቅ መነቃቃት መፍጠሩን የኢኮኖሚ ባለሙያው በረከት አድማሱ ይገልጻሉ፡፡
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት በረከት አድማሱ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ኢትዮጵያ ለዘመናት በልማዳዊ ግብርና ላይ ብቻ ተመስርታ መቆየቷን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተሞችና በክልሎች እየተስፋፉ ያሉ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስተሪዎች የምርትና ምርታማነት እድገት እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ሽግግር ለማፋጠን የተነደፈው ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀናት በፊት “የሉዓላዊነት ልብ” በሚል ርዕስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
ከመንግስት መር ወደ ግሉ ዘርፍ በተደረገው የኢኮኖሚ ሽግግር፣ በለውጡ መጀመሪያ 8 ሺህ ገደማ የነበሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በአሁኑ ወቅት ወደ 26 ሺህ ማደጋቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የገለጹት።
እንዲሁም የ”ስታርት አፕ” ስራዎች የተሰጣቸው ትኩረት ኢትዮጵያውያን በስፋት ተሰማርተው የሀገርን ኢኮኖሚ እንዲደግፉና ተወዳዳሪእንዲሆኑ የሚያስችል እንደሆነ የኢኮኖሚ ምሁሩ በረከት አድማሱ ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ማህበረሰቡ ከተለመደው አሰራር ወጥቶ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ላይ እንዲሰማራና ማነቆዎች እንዲፈቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰው ፣ ይህም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ለማድረስ ተስፋ ሰጪ እርምጃ መሆኑን በረከት አድማሱ አስገንዝበዋል።
ታደሠ ሽፈራው