የፌዴራል የስፖርት ልማት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ

You are currently viewing የፌዴራል የስፖርት ልማት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ

AMN – ሚያዝያ 13/2018 ዓ.ም

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል የስፖርት ልማት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡

የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ሪፖርትና ውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

የፌደራል ስፖርት ልማትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ በስፖርቱ ዘርፍ አካታች፣ አሳታፊ፣ ዘመናዊና አስተዳደራዊ የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት ምቹ መደላድል ይፈጥራል ተብሏል።

በዘርፉ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታና የስፖርት መሠረተ ልማትንና ማሰልጠኛ ተቋማትን በመገንባትና የስፖርት ግብዓት አምራቾችን እንደሚያበረታታም ተገልጿል።

አዋጁ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የራሱን ድርሻ ሊያበረክት የሚችል፤ በዜጎች መካከል ማህበራዊ ትስስርን የሚያጎለብት እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን የሚያጠናክር፤ ስፖርት ነክ ወንጀሎችን በመከላከል ስፖርትን ማስፋፋት የሚያስችል ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው የአዋጁን አስፈላጊት በሚመለከት አስተያየት ያቀረቡ ሲሆን አፈፃፀም ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ያሏቸውን ሀሳብ አቅርበዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በምክር ቤቱ አባላት ለተነሱት ሃሳቦች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

‎ስፖርት የኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ እንዲሆን ዘርፉን የያዙትን ማነቆዎች በአሰራርና ስርዓት መፍታት ያስፈልጋል ሲሉ የረቂቅ አዋጁን አስፈላጊነት ጠቁመዋል።

ስፖርቱ ዘርፍ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓትን የተከተለ እንዲሆን በማድረግ በዘርፉ ለሚስተዋሉ ማነቆዎች ምላሽ የሚሰጥና ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ በማድረጉ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለውም ገልፀዋል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1413/2018 አድርጎ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review