ዝምተኛው ገዳይ – ሄፓታይተስ ቢ ቫይረስ

You are currently viewing ዝምተኛው ገዳይ – ሄፓታይተስ ቢ ቫይረስ
  • Post category:ጤና

AMN – ሚያዝያ 15/2018 ዓ.ም

የሄፓታይተስ ቢ ቫይረስ (HBV) በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃና ለከፋ የጉበት ሕመም የሚዳርግ ዋነኛ የጤና ስጋት ነው።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ጠቅላላ ሐኪም ዶ/ር ሐሴት ለገሰ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ 254 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሲሆን፣ በየዓመቱ ደግሞ 1.1 ሚሊዮን የሚሆኑት ከሕመሙ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ሕይወታቸውን ያጣሉ።

በኢትዮጵያም ከ100 ሰዎች መካከል በአማካይ 7ቱ በቫይረሱ የተጠቁ መሆናቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ሐሴት፣ ይህም በሽታው በአገሪቱ ያለውን ከፍተኛ ስርጭት እንደሚያሳይ ጠቁማለች።

ቫይረሱ በዋነኝነት የሚተላለፈው ከእናት ወደ ልጅ በእርግዝና፣ በወሊድ ወቅትና ከወሊድ በኋላ በሚኖር ንክኪ እንደሆነ ባለሙያዋ ገልፀዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ ስለታም ነገሮችንና መርፌዎችን በጋራ መጠቀም እንዲሁም በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ደም ወይም የሰውነት ፈሳሾች ጋር የሚኖር ንክኪ ለበሽታው የሚያጋልጡ ዋነኛ መንገዶች መሆናቸውን ገልፀዋል።

በሽታው በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ምንም ዓይነት ምልክት ላያሳይ እንደሚችል የገለፁት ዶ/ር ሐሴት፣ በዚህም ምክንያት “ዝምተኛው ገዳይ” ተብሎ እንደሚጠራ ጠቅሰዋል።

ምልክቶች በሚታዩበት ወቅት ከፍተኛ ድካም፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የማቅለሽለሽ ስሜት፣ የሽንት ቀለም መጥቆር እንዲሁም የዓይንና የቆዳ ቢጫ መሆን ዋነኞቹ መገለጫዎች ናቸው።

የሄፓታይተስ ቢ ቫይረስ ኢንፌክሽን ሥር በሚሰድድበት ወቅት ለረጅም ጊዜ ለሚቆይ የጉበት በሽታ፣ ለጉበት ሥራ ማቆም እና ለጉበት ካንሰር ሊዳርግ ይችላል።

ይህንን አስከፊ የጤና ችግር ለመከላከል ነፍሰ ጡር እናቶች የእርግዝና ክትትል እንዲያደርጉና ቫይረሱ ካለባቸው እናቶች የሚወለዱ ሕፃናት በተወለዱ በ12 ሰዓታት ውስጥ ክትባቱን እንዲያገኙ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ባለሙያዋ አስገንዝበዋል።

ሄፓታይተስ ቢን በክትባት መከላከል የሚቻል በሽታ ሲሆን፤ ክትባቱ በሦስት ዙር የሚሰጥና ከ95 በመቶ በላይ የመከላከል አቅም እንዳለውም ዶ/ር ሐሴት ገልፀዋል።

ለቫይረሱ የሚሰጡ የፀረ-ቫይረስ መድኃኒቶች ቫይረሱ በጉበት ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት ለመቀነስና ወደ ካንሰር የመቀየር ዕድሉን ለማጥበብ ይረዳሉ።

የሕክምናው ዓይነት እንደ በሽታው ደረጃና በጉበት ላይ እንደደረሰው ጉዳት መጠን እንደሚወሰን የገለፁት ዶ/ር ሐሴት፣ ችግሮችን በጊዜ ለመለየትና ተገቢውን እንክብካቤ ለማግኘት ዘወትር የሕክምና ምርመራና ክትትል ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review