AMN-ሚያዝ 15/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያና የቱርክ የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነትን የሚያጠናከር የቢዝነስ ኮንፈረንስ እና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ተከፍቷል።
በቱርኩ የዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ ትብብር ፎረም እና በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አማካኝነት በተዘጋጀው 9ኛው የቢዝነስ ፎረም ከ50 በላይ የቱርክዬ ኢንቨስተሮች የተሳተፉበትም ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ የገበያ ማዕከል እየሆነች መምጣቷን ገልፀዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የረዥም ጊዜ ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የቱርክዬ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዎፆ እያበረከቱ መሆኑን የገለፁት አቶ ጃንጥራር፣ ይህ የቢዝነስ ፎረምም የቀደመውን ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ በዘርፉ አዳዲስ እድሎችን ለመፍጠር ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
የቱርክዬ የዓለም አቀፍ ኢንዱስትሪ ፕሬዚዳንት ኡቱኩ ቤንጋሲ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በኢንቨስትመንትና በንግድ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ሀገራት መካከል መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የንግድ አጋራችን ናት ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ይህ ጥብቅ ትብብር ትልቅ ለውጥ ያመጣል ሲሉም ተናግረዋል።
ለሁለት ቀን በሚቆየው የቢዝነስ ፎረም ላይ በዘርፉ የተሠማሩ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
በፀጋ ታደለ