AMN- ግንቦት 02/2018 ዓ.ም
የእናቶች ቀን አከባበር ታሪክ አመጣጥ ሲታይ፣ በዘመናዊ መልኩ እውቅና ያገኘው በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በአሜሪካዊቷ አና ጃርቪስ ጥረት ነው።
አና እናቷን ካጣች በኋላ፣ እናቶች ለልጆቻቸውና ለቤተሰባቸው የሚከፍሉትን ወደር የለሽ መስዋዕትነት ዓለም እንዲያውቀውና እውቅና እንዲሰጥ ባደረገችው ከፍተኛ ትግል፣ እ.ኤ.አ. በ1914 በይፋ እንዲከበር ተወሰነ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ በግንቦት ወር ሁለተኛ ሳምንት እሁድ፣ ዓለም የእናቶችን ቀን በልዩ ድምቀት ማክበር ጀመረች።
በኢትዮጵያም ይህ ቀን በልዩ ስሜት ይከበራል።
በተለይ በሀገራችን የጥበብ ዓለም ውስጥ እናት የቋሚ መሪ ርዕስ ነች።
ገጣሚያንና ድምፃውያን ስለ እናት ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር፣ ናፍቆትና ምስጋና የሚገልጹት በቃላት ብቻ ሳይሆን፣ ልብ በሚነካ ዜማና በረቀቀ የቅኔ ቋጠሮ ነው።
ለኢትዮጵያዊያን “እናት” ከወላጅነትም በላይ “ሀገር” ናት፤ መከራን የምታሸንፍ፣ ጥጥ ፈትላ የምታለብስና በባዶ ሆዷ ልጆቿን የምታጠግብ የጽናት ተምሳሌት ተደርጋ ትሳላለች።
ዓለም አቀፍ የእናቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የማይረሱና የእናትን ክብር የዘከሩ የጥበብ ስራዎች ዛሬም በብዙዎች ዘንድ በታላቅ ስሜት እየተሰሙ ይገኛሉ።
በተለይም የድምፃዊ ይርዳው ጤናው “እናቴነሽ ዓለም” እና የብዙነሽ በቀለ “የእናት ወለታዋ” የተሰኙ ስራዎች የእናትን ልዩ ቦታና የማይከፈል ውለታን በመግለጽ ረገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው።
የእናትነት ትርጉም በ”እናቴነሽ ዓለም”
ድምፃዊ ይርዳው ጤናው በዜማው እንደገለጸው፤ እናት ለአንድ ሰው መላው ዓለሙ፣ የህይወቱ መሠረትና የፍቅር ምንጭ ናት። “እናቴነሽ ዓለሜ” የሚለው መልእክቱ እናት ከቃል በላይ የሆነች፣ ለልጆቿ ስትል መስዋዕትነትን የምትከፍልና በምንም የማይተካ የህይወት ምሰሶ መሆኑን ያጎላል።
ሙዚቃው ዛሬም ድረስ የእናቶችን ቀን በልዩ ሁኔታ የሚናኝ እና የሚደመጥ ሙዚቃ ነው።
“የእናት ወለታዋ” እና የማይከፈለው ዕዳ
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንግሥት ብዙነሽ በቀለ “የእናት ውለታዋ” በሚለው ዝነኛ ስራዋ፤ አንዲት እናት ከፅንሥ ጀምሮ እስከ እድገት ድረስ የምታሳልፈውን እልህ አስጨራሽና ፍቅር የተሞላበት ጉዞ በዝርዝር ታሳያለች።
የእናት ውለታ በገንዘብም ሆነ በቁሳቁስ የማይመጥን መሆኑን የሚያወሳው የብዙነሽ ሙዚቃ፤ እናትን ማክበርና መንከባከብ የሰው ልጅ ትልቁ ግዴታ መሆኑን በዜማዋ ታስተምራለች።
እነዚህ የጥበብ ስራዎች እናት ለሀገርና ለወገን የምታበረክተውን አስተዋጽኦ የሚያንፀባርቁ ሲሆን፣ የእናቶች ቀን ሲከበርም እነዚህን የቆዩ ግን የማይረሱ እሴቶችን በማስታወስ መሆን እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ዛሬም ድረስ እነዚህ ሙዚቃዎች በልጆችና በወላጆች መካከል ያለውን ጥልቅ ትስስር በማጠናከር በኩል ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። ይህ የግጥም ቋጠሮ ልጆች ለወላጆቻቸው ያላቸውን የዘላለም ዕዳና ታላቅ አክብሮት በግልጽ ያሳያል።
በአጠቃላይ፣ የእናቶች ቀን በኢትዮጵያ ድምፃውያን አንደበት ሲገለጽ የፍቅር፣ የጽናትና የሀገር ታሪክ ሆኖ እናገኘዋለን። እነዚህ የጥበብ ሰዎች የቀረጹት የዜማ ስንኝ፣ እናት በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ያላትን ስር የሰደደ ስፍራ ይመሰክራል።
እናቶች የህይወት ምንጭ ብቻ ሳይሆኑ፣ የባህልና የሞራል መሠረቶች በመሆናቸው፣ ሁሉም ቀን የእነሱ ቢሆን አያንሳቸውም ።
እናንተስ የእናቶችን ቀን እንዴት አከበራችሁን? አጋሩን።
በያለው ጌታነህ