AMN – ግንቦት 3/2018 ዓ.ም
የጤና ሚኒስቴር ከ32 ሚሊየን በላይ ዜጎች የጤና መረጃ ዲጂታል ማድረጉን አስታወቀ።
5ኛው ብሔራዊ የመረጃ እና የዲጂታል ጤና ሳምንት “በጤና መረጃ እና በዲጂታል ጤና ፈጠራዎች ላይ በዘላቂ ኢንቨስትመንት የጤና ትሩፋቶችን ማሳደግ” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ፤ ዲጂታላይዜሽን የጤናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የሀገራችን አጠቃላይ የትራንስፎርሜሽን ጉዞ ዋና ምሰሶ መሆኑን በመግለጽ የዲጂታል የመረጃ ስርዓት ግልፅነትንና ተጠያቂነትን ለማጠናከር የሚያገለግል ሀገራዊ አቅጣጫ ነው ብለዋል።

በዲጂታል የጤና ስርዓቱ ከ47 በላይ የዲጂታል ጤና መሳሪያዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በስራ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከ3 ሺህ 500 በላይ የጤና ተቋማት በ“ ሄልዝኔት”ተገናኝተዋል።
ከ227 በላይ ተቋማት የ “ኤሌክትሮኒክ ሜዲካል ሪከርድ” ስርዓትን በሙሉ ተግባራዊ አድርገዋል።
በስነ-ህዝብ ጤና በ418 ወረዳዎች ከ32 ሚሊየን በላይ ቤተሰቦችን ዲጂታል ስለመደረጉም የጤና ሚንስትሯ ተናግረዋል።

በቀጣይም ወደ ጤና ስርዓቱ የሚገቡ የጤና መረጃዎችን በመለየት እንዲናበቡ ማድረግ እንደሚገባ ዶ/ር መቅደስ አሳስበዋል።
በመድረኩ ዶ/ር መቅደስ ዳባን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የስድስት ዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮች፣ የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎችና የጤና ስርዓት መረጃ ባለሞያዎች ተገኝተዋል።
በወንድምአገኝ አበ