የኮደርስ ስልጠና የወጣቶችን ዲጂታል ክህሎት ከመገንባት ባለፈ ሰልጣኞች ለአዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ዝግጁ እንዲሆኑ እያደረገ ነው

You are currently viewing የኮደርስ ስልጠና የወጣቶችን ዲጂታል ክህሎት ከመገንባት ባለፈ ሰልጣኞች ለአዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ዝግጁ እንዲሆኑ እያደረገ ነው

AMN – ግንቦት 3/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ እየተሰጠ ያለው የኮደርስ ስልጠና የወጣቶችን ዲጂታል ክህሎት ከመገንባት ባለፈ ሰልጣኖች ለአዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ዝግጁ እንዲሆኑ እያደረገ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የከተማዋ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አዋሌ መሐመድ ለኤ ኤም ኤን እንዳሉት፤ የ5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭ ዲጂታል ክህሎትን ለመገንባት አጋዥ ነው፡፡

በዚህም ተቋማቸው ስልጠናውን በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ከሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው ወጣቶች፣ ተማሪዎች እና የመንግስት ሰራቶች እየተሳተፉ ሲሆን የ5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በአራት ዘርፎች ላይ ትኩረት ተደርጎ በኦንላይን እየተሰጠ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡

በከተማዋ ለ809 ሺህ 251 ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና ለመስጠት መታቀዱን በማስታወስ ከ900 ሺህ በላይ ሰልጣኞች እንደተመዘገቡና 678 ሺህ የሚሆኑት ስልጠናውን መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።

በተለይም ወጣቱ በፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንዲሆን ትኩረት ተደርጓል ያሉት የቢሮ ሃላፊው፤ ሥልጠናው ዜጎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መሰረት የሚጥል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ስልጠናው ዜጎች የእለት ከእለት ሥራዎችን በቀላሉ እንዲያከናውኑ ተጨማሪ አቅም ከመፍጠር ባለፈ የሃገር ኢኮኖሚ ለመገንባትም ጉልህ ሚና እንደሚጫዎት ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡

ኢኒሼቲቩ ወደ ዲጂታል እየሄደ ያለው ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ ወጣቱ የራሱን ድርሻ እንዲያበረክት፣ ቱሪዝሙ፣ ኢንዱስትሪው እና ግብርናውም በቴክኖሎጂ እንዲደገፍም ይረዳል ብለዋል፡፡

ዲጂታል ሥልጠናው ለሌሎች ሃገራት ኢኮኖሚ ማደግና መለወጥ ምክንያት እየሆነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ እየተሰጠ ያለው ስልጠናም ሃገሪቱ ከሌላው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን ከማድረግ ባለፈ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ እንደሚረዳ በመግለጸ፤ ዜጎች የዲጂታል በቂ እውቀት ይዘው የሞባይል መተግበሪያዎችንም በቀላሉ ተረድተው እንዲጠቀሙ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የኮደርስ ስልጠና የወጣቶችን ዲጂታል ክህሎት ከመገንባት ባለፈ ሰልጣኞች ለአዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ዝግጁ እንዲሆኑ እያደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡

በየሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review