አዲስ አበባ የነገዋን ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት “የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራምን” በስፋት እያከናወነች ነው

You are currently viewing አዲስ አበባ የነገዋን ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት “የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራምን” በስፋት እያከናወነች ነው

AMN – ግንቦት 3/2016 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የነገዋን ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባትና የከተማዋን ቀጣይ ትውልድ ስብዕና ለመቅረፅ የሚያስችለውን “የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም” በልዩ ትኩረት እየተገበረ ይገኛል።

የከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥንስስ የሆነውና በአዲስ አበባ የተጀመረው ይህ ፕሮግራም፣ ሕፃናት ገና በማህፀን ውስጥ ካሉበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ስድስት ዓመት እድሜያቸው ድረስ ያለውን ወሳኝ የዕድገት ዘመን ታሳቢ ያደረገ ሁለንተናዊ እንክብካቤን ማዕከል ያደረገ ነው።

አስተዳደሩ ለዘርፉ ስኬታማነት ሰፋፊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችንና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በቅንጅት እያከናወነ ይገኛል።

በሁሉም የከተማዋ ክፍለ ከተሞች ሕፃናት ቦርቀው የሚጫወቱባቸውና ማህበራዊ ትስስርን የሚለማመዱባቸው ከ5 ሺህ በላይ የመጫወቻ ስፍራዎች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ወላጆችና አሳዳጊዎች ልጆቻቸውን የሚያውሉበት ቦታ እንዳይቸገሩ ለማድረግ፣ አስፈላጊው እንክብካቤ የሚደረግላቸው ከ1000 በላይ የሕፃናት ማቆያዎች (ዴይ ኬር) ተገንብተው በርካታ ወላጆችና ሕፃናትን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል።

በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እናቶች በሥራ ገበታቸው ላይ ሆነው ልጆቻቸውን በቅርበት እንዲንከባከቡና በሥራቸው ላይ ሙሉ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚያስችሉ 713 የሕፃናት ማቆያዎች ከተማዋ በፊዴራል ተቋማትን ጨምሮ የተደራጁ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በከተማዋ ከአሥራ አንድ ሺህ በላይ ሕፃናት በማቆያዎቹ ውስጥ አገልግሎት በማግኘት ላይ ይገኛሉ።

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ልጆች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳይጎዱ በትምህርት ቤቶችና በማዕከላት የምግብ አቅርቦት ተመቻችቷል።

ይህ የአዲስ አበባ ተሞክሮ እንደ ብራዚል፣ ኮሎምቢያ እና ሲንጋፖር ያሉ ሀገራት የሚተገብሯቸውን ምርጥ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ስኬት ለዓለም የምታሳይበት ታላቅ መድረክም ተመቻችቷል።

“አፍሪካ በቀዳማይ ልጅነት ሥርዓተ ለውጥ የግንባር ቀደምትነት ሚና ከአካባቢያዊ ሞዴሎች ወደ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ” በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከግንቦት 3 እስከ 5 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

መድረኩ አዲስ አበባ በእናቶችና ሕፃናት ጤና፣ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት መስፋፋት እና በሕፃናት ማቆያ አገልግሎት ያላትን ምርጥ ተሞክሮ የምታካፍልበት ከመሆኑም ባለፈ፣ በዘርፉ የሚስተዋሉ የፋይናንስና የአመራር ክፍተቶችን በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት የሚያግዝ የልምድ ልውውጥ ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review