AMN – ግንቦት 13/ 2018 ዓ.ም
የኑሮ ውድነትና የገበያ መዛባት ዓለም አቀፍ ክስተት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ሃገራትም ይህንኑ የኑሮ ዉድነትና የገበያ መዛባት ለመቋቋም የተለያዩ እርምጃዎችን በመዉሰድ ላይ የሚገኙ ሲሆን በኢትዮጵያም የኑሮ ጫናዉን ለመቀነስ በርካታ የመፍትሔ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ፡፡
በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ የቁጥጥር ሥርዓት ከመዘርጋትና የምርት አቅርቦትን ከማሳደግ ባለፈ ተኪ ምርቶች በብዛትና በጥራት እንዲመረቱ ተገቢዉን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በመዲናዋ በሚገኙ በአምስቱም መግቢያ በሮች ስድስት የገበያ ማዕከላትንና የእሁድ ገበያዎችን በተለያዩ የከተማው ቦታዎች በመክፈት ነዋሪዎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
አቅመ ደካማ፤ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች ያሉባቸዉን የኑሮ ጫና ለመቀነስ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች 29 የምገባ ማዕከላት በመክፈት ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ የምገባ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የዜጎችን ክብር በመጠበቅ ላይ ይገኛል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በመካከለኛዉ ምስራቅ ከተከሰተዉ የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ሊከሰት የሚችለዉን የኑሮ ውድነትና የገበያ መዛባት ለመቋቋም ነዳጅን በቁጠባ ከመጠቀም ጀምሮ ጥብቅ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ስርዓትን በመዘርጋት፤ በምርቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት በመቆጣጠርና በህገ ወጦች ላይ እርምጃ በመዉሰድ የገበያ ማረጋጋት ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማዉ ምክር ቤት በቅርቡ ባካሄደዉ 5ኛ አመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ከተማ አስተዳደሩ የበጎ ፈቃድ አገልገሎቶችን ጨምሮ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ከሚያከናዉናቸዉ ሰዉ ተኮር ስራዎች በተጨማሪ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 18 ቢሊዮን ብር በተለያዩ ዘርፎች ላይ ድጎማ በማድረግ የነዋሪዎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ በመስራት ላይ እንደሚገኝ መግለጻቸዉ ይታወሳል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከዓለም አቀፍ ክስተት ጋር ተያያዥነት ያለዉን ይህንኑ የኑሮ ዉድነትና የገበያ መዛባት ለመቋቋም የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ በምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት በየደረጃዉ ከሚገኙ የከተማዉ አመራሮች ጋር የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ፣ ገበያን ለማረጋጋት እና ለማረቅ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ገምግመዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ግምገማዉን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት በመደበኛው አሰራርም ሆነ በመሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል የአገልግሎት አሰጣጥ በታቀደዉ መሰረት መሻሻል መታየቱን ገልጸዋል፡፡

የኑሮ ውድነት ጫናን ቀነስ፣ ገበያን ለማረጋጋት እና ለማረቅ እየተከናወነ የሚገኘዉ ስራ በአብዛኛው ውጤታማ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በነዳጅ ምክንያት የዋጋ ጭማሪ የታየባቸዉ የአንዳንድ ሸቀጦች ዋጋ ግን አሁንም በተሟላ ሁኔታ እንዳልወረደ ተረድተናል ብለዋል፡፡
በዘርፉ የሚታየዉን ዉስንነት ለማስተካከል የሚወሰዱ አንዳንድ የማስተካከያ እርምጃዎችም ተጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በተለያዩ መንገዶች ከሚወስዳቸዉ የመፍትሔ እርምጃዎች በተጨማሪ በቤት ልማት፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በምገባ ማዕከላት፣ በተማሪዎች ምገባ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በጤና መድን አገልግሎት፣ በከተማ አውቶብስ አቅርቦት፣ በፐብሊክ ትራንስፖርት አቅርቦትና በተለያዩ መንገዶች የድጎማ ስርዓትን ዘርግቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ