AMN – ግንቦት 17/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባን ቀደም ሲል ከነበረችበት የዲፕሎማሲ መናገሻነት እና የትራንዚት ከተማነት ባለፈ፣ ተመራጭና ተወዳዳሪ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ባለፉት ጥቂት ዓመታት መጠነ-ሰፊ እና ስትራቴጂካዊ የሆኑ ሥራዎች ተከናውነዋል።
ከተማዋን ለማዘመን፣ ታሪካዊ ቅርሶቿን ለመጠበቅ እና አዳዲስ ሰው ሰራሽ መስህቦችን ለመፍጠር በርካታ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ አመርቂ ስኬቶችም ተመዝግበዋል።

የከተማዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ የቀየሩና የቱሪስት ፍሰትን የሳቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል።
ከእነዚህም መካከል፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትኩረትን የሳበ፣ ዘመናዊና ልዩ የስነ-ህንጻ ጥበብ ያረፈበት የቴክኖሎጂና የፈጠራ ማዕከል የሆነው የሳይንስ ሙዚየም አንዱ ነው።
የሀገሪቱን የፖለቲካ፣ የታሪክና የባህል ጉዞ የሚያሳይ፣ የዱር እንስሳት ማቆያና ታሪካዊ ህንጻዎችን ያቀፈ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ የሆነው አንድነት ፓርክ (ታላቁ ቤተ-መንግስት) ሌላኛው ተጠቃሽ ፕሮጀክት ነው።

ከተማዋን ከተፈጥሮ፣ ከስፖርት፣ ከባህልና ከዘመናዊ መዝናኛዎች ጋር ያስተሳሰረው የተፈጥሮ መስህብ እንጦጦ ፓርክ፣ በከተማዋ እምብርት ላይ የሚገኝ፣ ሰው ሰራሽ ሐይቅ፣ የውሃ ትርዒት እና ለተለያዩ ሁነቶች የሚሆን ዘመናዊ አደባባይ የሸገር ፓርክ (ወዳጅነት አደባባይ) ተጠቃሾች ናቸው።
የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት የሆነውን የዓድዋ ድል ታሪክ፣ ቅርሶችና ሥነ-ጥበባትን በዘመናዊ መልኩ የሰነደ፣ ለጎብኚዎች ትልቅ የእውቀትና የታሪክ ማዕከል የሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያም አንዱ መስህብ ነው።
የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት፣ የውበትና የጽዳት ደረጃ ዓለም አቀፍ ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራም ትልቅ ስኬት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለከተማው ምክር ቤት ዓባላት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት መግለፃቸው ይታወሳል።

ሰፋፊ የእግር መንገድ እና የብስክሌት መስመሮች መገንባታቸውን፣ የከተማዋ ታሪካዊ ህንጻዎችና ቅርሶች ማንነታቸው ሳይቀየር እድሳት መደረጉ እና አረንጓዴ ስፍራዎች፣ የውሃ መዝናኛዎች እና ማራኪ የብርሃን ዲዛይኖችም በስፋት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
የዲጂታል ቱሪዝም እና መሰረተ-ልማት ማሻሻያ በማካሄድም፣ የኢ-ቪዛ (E-visa) እና የከተማዋን የዲጂታል መረጃ አቅርቦት በማዘመን የጎብኚዎችን እንግልት መቀነስ ተችሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን በማስፋፋት እና ዘመናዊ የሆቴል አገልግሎቶችን በማቅረብ የትራንዚት ተጓዦች ወደ ከተማዋ ገብተው እንዲጎበኙ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
በዚህም ቀደም ሲል ቱሪስቶች አዲስ አበባን እንደ መተላለፊያ ብቻ ይጠቀሙባት ከነበረበት፣ አሁን ላይ በአማካይ ከ3 እስከ 5 ቀናት በከተማዋ እንዲቆዩ የሚያስችሉ መስህቦች ተፈጥረዋል።

አዲስ አበባ ከአፍሪካ ህብረት እና ከተመድ (UNECA) መቀመጫነቷ በተጨማሪ፣ ባሏት አዳዲስ አዳራሾችና መሰረተ-ልማቶች ምክንያት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን፣ ኤግዚቢሽኖችንና የንግድ ትርኢቶችን የማስተናገድ አቅሟ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።
የቱሪስት መዳረሻዎቹ መበራከት ለሆቴሎች፣ ለትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ ለባህል አልባሳትና ቅርፃቅርፅ አምራቾች እንዲሁም ለተንቀሳቃሽ ምስልና ፎቶ አንሺዎች ሰፊ የሥራ ዕድልና የገቢ ምንጭ ፈጥሯል።
በአጠቃላይ፣ በአዲስ አበባ የተከናወኑት የቱሪዝም ሥራዎች ከተማዋን የዲፕሎማሲ መናገሻ ብቻ ሳትሆን፣ የባህል፣ የታሪክ፣ የቴክኖሎጂ እና የተፈጥሮ ውበት መገናኛ ድንቅ የአፍሪካ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን አድርገዋታል።
በታምራት ቢሻው