ከተሻሻለው የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ ጋር ተያይዞ ያጋጠመዉን የአገልግሎት መስተጓጎል ለመፍታት እየሠራ መሆኑን ባንኩ አስታወቀ

You are currently viewing ከተሻሻለው የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ ጋር ተያይዞ ያጋጠመዉን የአገልግሎት መስተጓጎል ለመፍታት እየሠራ መሆኑን ባንኩ አስታወቀ

AMN- ግንቦት 20/2018 ዓ.ም

ከተሻሻለው የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ ጋር ተያይዞ ያጋጠመዉን የአገልግሎት መስተጓጎል ለመፍታት እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግሎቱን ቀላል፣ ምቹ እና በማንኛውም ሰዓት ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ የዲጂታል አገልግሎት አማራጮችን በየጊዜው ለደንበኞቹ እንደሚያቀርብ አስታዉቋል።

ከእነዚህ የዲጂታል አገልግሎት አማራጮች መካከል ደግሞ ደንበኞች ሒሳባቸውን በቀላሉ፣ በማንኛውም ሰዓትና ቦታ በስልካቸው ማንቀሳቀስ ያስቻላቸው የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ዋነኛው ነው።

ባንኩ የደንበኞችን የአገልግሎት እርካታ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በየጊዜው ሥርዓቱን የሚያዘምን መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በርካታ አዳዲስ የአገልግሎት አማራጮችን በማካተት እንዲሁም ለአጠቃቀም ምቹና ቀላል በማድረግ የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያውን አሻሽሎ ማቅረቡን አስታዉቋል።

በዚህ መሠረት የተሻሻለውን የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ በርካታ ደንበኞች እየተጠቀሙበት የሚገኝ ሲሆን፣ መተግበሪያው አዲስ በመሆኑ ምክንያት በተወሰኑ ደንበኞች ላይ የአገልግሎት መስተጓጎል እንዳጋጠመ መረዳቱን ገልጿል።

ለተፈጠረው የአገልግሎት መስተጓጎል ይቅርታ የጠየቀዉ ባንኩ፣ ችግሩን በአፋጣኝ ለመፍታት ርብርብ እየተደረገ መሆኑንና እንደተፈታም ለደንበኞቹ የሚያሳዉቅ መሆኑን ገልጿል።

ከተሻሻለው መተግበሪያ ጋር በተያያዘ ችግር ያጋጠማቸዉ ደንበኞች ከታች በተቀመጠው ማስፈንጠሪያ (ሊንክ) በመግባት፣ ወደ 951 ነጻ የደንበኞች ጥሪ ማዕከል በመደወል ወይም በባንኩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች በኩል መልዕክት በመላክ ድጋፍ ማግኘት የሚችሉ መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review