ማለዳ መነሳት የጤናማ ሕይወት ቁልፍ ሚስጥር

AMN – ግንቦት 22/2018 ዓ.ም

በጠዋት መነሳት ለብዙዎቻችን ፈታኝ ቢሆንም፣ ለአጠቃላይ ሕይወታችን ስኬትና ጤና ያለው ጠቀሜታ ግን እጅግ የላቀ መሆኑ ይነገራል።

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ብሩክ አለማየሁ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ማለዳ መነሳት ስላለው ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞች ሳይንሳዊ ማረጋገጫዎችን በመጥቀስ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዶ/ር ብሩክ እንደሚያስረዱት፣ ማለዳ የሚነሱ ሰዎች በጤና፣ በምርታማነት እንዲሁም ሕይወታቸውን በራሳቸው ዕቅድ የመምራትና የመቆጣጠር ከፍተኛ ብልጫ አላቸው።

እነዚህ ሰዎች ያቀዷቸውን ዓላማዎችና ግቦች የማሳካት ዕድላቸው እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ፣ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ፈታኝ ሁኔታዎችን የመቋቋም፣ የመጋፈጥ እና የመቆጣጠር ብቃታቸው የላቀ ነው።

ዶ/ር ብሩክ አክለውም፣ ወደ ስምንት መቶ አርባ ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ያካተተ አንድ ጥናት ያስገኘውን አስገራሚ ውጤት ጠቅሰው፣ ማለዳ የሚነሱ ሰዎች በዲፕሬሽን ወይም በድብርት የመጠቃት ዕድላቸው በሃያ ሶስት በመቶ እንደሚቀንስ ጥናቱ ማረጋገጡን ገልጸዋል።

ዶ/ር ብሩክ በአሜሪካ የተሠራን ሌላ ጥናት ዋቢ በማድረግ እንደገለጹት፣ በማለዳ ተነሥቶ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ሙሉ ቀኑን በከፍተኛ መነቃቃት ለማሳለፍ ይረዳል።

ይህ ልማድ በሰውነታችን ውስጥ ያለውን ከመጠን ያለፈ ስብ ለማቃጠል ከማገዙም በላይ፣ ለስኳር በሽታ አጋላጭ የሆነውን የኢንሱሊን ሚዛን መዛባትን ችግር ይቀንሳል።

ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ማኅበረሰቡን በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቁ ያሉትን እንደ ስኳር እና ኮሌስትሮል ያሉ የሜታቦሊክ በሽታዎች የመከሰት ዕድላቸውን በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ እንደሚያደርገው ዶ/ር ብሩክ አብራርተዋል።

ማለዳ መነሳት “ቀኑ ሳይጀምር መነሳት” እንደመሆኑ መጠን፣ ሥራን በአግባቡ ለማቀድና ውጤታማ ለመሆን ትልቅ ዕድል ይሰጣል።

በአንጻሩ ዶ/ር ብሩክ አርፍደው ስለሚነሱ ሰዎች ሲያስረዱ፣ አርፍደን መነሳት ቀኑ ቀድሞ ስለሚያልፍ ውሎው የሚያልፈው በውክቢያ ውስጥ ሆኖ ነው ይላሉ።

አርፍደው የሚነሱ ሰዎች ያመለጣቸውን ሰዓት ለማካካስ ሲሯሯጡ የሚውሉ ሲሆን፣ የትናንት የተከማቸ ሥራን ዛሬ ለመሥራት በመጨነቅ በመጨረሻም ሥራቸውን ሳይጨርሱ ማታ በብስጭት ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ።

ይህ ሁኔታ በተደጋጋሚ ሲከሰት ደግሞ የሰዎችን ተነሳሽነት በመግደል የስራ ውጤታማነትንና የሕይወት ደስታን ሙሉ በሙሉ ሊያሳጣ ይችላል።

ማለዳ ላይ መነሳት ለአካላዊ፣ ለአእምሮአዊና ለስነ-ልቦናዊ ጤናችን በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት የገለጹት ዶ/ር ብሩክ፣ ሕይወታችን በውክቢያ ሳይሆን በሰላምና በእቅድ ይመራ ዘንድ፣ እንዲሁም ከስኳር፣ ከኮሌስትሮልና ከድብርት በሽታዎች ራሳችንን ለመጠበቅ ማለዳ መነሳትን የዘወትር ልማዳችን ልናደርገው ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review