AMN – ግንቦት 29/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ የተገነቡ፣ እድሳትና ማስፋፊያ የተደረገላቸው ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ወረቀት አልባ የጤና አገልግሎት አሰራርን እየተገበሩ ይገኛል፡፡
የጤና ጣቢያዎቹ የሥራ ኃላፊዎች ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደገለጹት ፤ ለዜጎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት የጤና ተቋማትን ማዘመንና ወረቀት አልባ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
በዚህም በመዲናዋ አዲስ የተገነቡ፤ እድሳትና እና ማስፋፊያ የተደረገላቸው ጤና ጣቢያዎች ወረቀት አልባ የጤና አገልግሎት አሰራርን እየተገበሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በጤና ጣቢያዎች ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው ዲጂታል አሰራር የተገልጋዮችን ፍላጎት እያሟላና የታካሚዎች እንግልት እንዳይፈጠር እገዛ እያደረገ ስለመሆኑም ኃላፊዎች አንስተዋል፡፡

ወረቀት አልባ የጤና አገልግሎት እየተሰጠባቸው ከሚገኙት ጤና ጣቢያዎች መካከል የአቃቂ ቃሊቲ ጤና ጣቢያ እና አስኮ አዲስ ሰፈር ጤና ጣቢያዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የአቃቂ ቃሊቲ ጤና ጣቢያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታሁን ዋቅጋሪ፤ ጤና ጣቢያው ለተገልጋዮች ዲጂታል በሆነ አሰራር አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጤና ጣቢያው ከሶስት በላይ ለሆኑ ወረዳዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን በማንሳት በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት እያገኘ ነው ብለዋል፡፡
የአስኮ አዲስ ሰፈር ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር ዩሱፍ ቱግባር በበኩላቸው፤ በጤና ጣቢያው አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በማሟላት ወረቀት አልባ አገልግሎት ተጀምሯል ነው ያሉት፡፡
ይህ የወረቀት አልባ አገልግሎት የተገልጋይ መረጃ እንዳይጠፋና እንዳይበላሽ እንዲሁም በጥራት እንዲያዝ ይረዳል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም አሰራሩ ወደ ጤና ተቋማቱ የሚሄዱ ተገልጋዮች ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ እየረዳ መሆኑን በመግለጽ አገልግሎትን ወደ ወረቀት አልባ ማምጣት መንግስት ትኩረት አድርጎ እየሰራበት ያለ ጉዳይ መሆኑንም አቶ ዩሱፍ ቱግባር አስገንዝበዋል፡፡

በጤና ጣቢያዎቹ ተግባራዊ የተደረገው የወረቀት አልባ የህክምና አሰራር ለስራው ውጤታማነት ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ሲሆን የወረቀት አልባ አሰራር ወጪንም ይቆጥባል ብለዋል፡፡
እንደ ዩሱፍ ቱግባር ገለጻ፤ ዲጂታል አሰራር ለህትመት የሚወጣውን የገንዘብ መጠንም በመቀነስ መድኃኒትንና ሌሎች መሰል ግብአቶችን ለመግዛት የሚያስችል ይሆናል፡፡
በጤና ጣቢያዎች ያለው የወረቀት አልባ የህክምና አገልግሎት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን የሚያሳድግና ለሰው ልጅ ጤና መሻሻልም አዎንታዊ አስተዋጽኦ አለው፡፡:
በዚህም የተገልጋዮችን ፍላጎት ለማሟላትና የታካሚዎች እንግልት እንዳይፈጠር ጤና ጣቢያዎቹ የወረቀት አልባ የህክምና ስርዓትን እየተገበሩ ይገኛል፡፡
የሻምበል ምህረት