ማዕከሉ ለዲኤንኤ እና ፎረንሲክ ምርመራዎች ወደ ውጭ ሀገር ለመጓዝ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪና እንግልት ያስቀራል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing ማዕከሉ ለዲኤንኤ እና ፎረንሲክ ምርመራዎች ወደ ውጭ ሀገር ለመጓዝ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪና እንግልት ያስቀራል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

​AMN – ግንቦት 30/2018 ዓ.ም

​የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ዘመናዊ የዲኤንኤ (DNA)፣ የፎረንሲክና ስነምረዛ ምርመራ የልህቀት ማዕከል በዳግማዊ ሚኒሊክ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በይፋ አስመርቋል።

ማዕከሉን መርቀው የከፈቱት የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ማዕከሉ ከዚህ ቀደም ለዲኤንኤ እና ለፎረንሲክ ምርመራዎች ወደ ውጭ ሀገር ለመጓዝ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪና እንግልት ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር መሆኑን ገልጸዋል።

​ይህ አዲስ የልህቀት ማዕከል ዘመናዊ የፎረንሲክ ኬሚስትሪ እና ቶክሲኮሎጂ ላቦራቶሪ የተሟላለት ሲሆን፣ ቀደም ሲል በሕክምና ተቋማት ለመለየት አስቸጋሪ የነበሩ በጣም አነስተኛ መርዞችን፣ መድኃኒቶችንና አልኮልን በቀላሉ ለመለየት ያስችላል።

ማዕከሉን ይበልጥ ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ቀደም ሲል ሳምንታትን ይወስድ የነበረውን የናሙና ትንተና ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ጋር በተሳሰሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመታገዝ በግማሽ ሰዓት ውስጥ ማከናወን ማስቻሉ ነው።

በተጨማሪም በአንድ ጊዜ 80 አስክሬኖችን ማቀዝቀዝና ማስቀመጥ የሚችል ሲሆን፣ 8 አውቶማቲክ ማሽኖችንና ተንቀሳቃሽ የራጅ መሳሪያዎችን አካቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

​ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፤ ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በከፍተኛ ደረጃ ከመመለስ ባለፈ ዜጎች ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ፍለጋ ወደ ውጪ ሀገር የሚጓዙበትን ሁኔታ እንደሚያስቀር አብራርተዋል።

አክለውም በሀገሪቱ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ሰራተኞች፣ ቱሪስቶችና ባለሀብቶች አስተማማኝ ሕክምና በሀገር ውስጥ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

​ይህ ስራ የኢትዮጵያን አዲስ ብልጽግና፣ የእድገት እና የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ምዕራፍ በማብሰር ሂደት ብዙ መንገድ የተሻገረን መሆናችንን የሚያሳይ ደማቅ ተግባር ነው ሲሉ ከንቲባዋ ተናግረዋል።

​ማዕከሉ ከተማ አስተዳደሩ ከሕዝብ የሰበሰበውን ግብር በታማኝነት ለሕዝብ አገልግሎት ማዋሉን የሚያሳይ ትልቅ ማሳያ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በከፍተኛ ልህቀት ደረጃ ከተገነቡ አራት አዳዲስ ሆስፒታሎች መካከል ሁለቱ በአሁኑ ወቅት ወደ ስራ መግባታቸውንና ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ በቅርቡ አገልግሎት እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።

​የከተማ አስተዳደሩ ከአክሞ ማዳን ተግባር ባሻገር በሽታን ቀድሞ የመከላከል ስራ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ፣ ከተማዋን ንጹህ፣ ለመኖር ምቹ እና ከብክለት የጸዳች በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝም በዚሁ ወቅት ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።

​በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review