AMN – ሰኔ 1/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያዊያን በመረጡበትና ኢትዮጵያ ባሸነፈችበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ፣ የተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በምርጫ ታዛቢነት ያሳዩት የነቃ ተሳትፎ ለዲሞክራሲ ሥርዓቱ ግንባታ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱ ተገለጸ።
የምርጫ ሂደቱን በማስመልከት የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ድርጅት ኅብረት እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ምርጫው ኢትዮጵያዊያንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ለጠንካራ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳዩበት መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን እንዳሉት፣ ይህ ምርጫ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማስፈጸም አቅም በተግባር የታየበትና ዲሞክራሲያዊነቱ የተረጋገጠበት ኩነት ነው።
አጠቃላይ ማኅበረሰቡ በነቂስ ወጥቶ እንዲመርጥ የሆነበት መሠረታዊ ምክንያት ሕዝቡ ሰላምንና የዲሞክራሲ ባህል መሻሻልን እንደሚፈልግ የታዘብንበት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የሚዲያው፣ የጸጥታ አካላትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅንጅት ለጠንካራ መንግሥት ግንባታና ሀገርን ለማስከበር ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ድርጅት ኅብረት ዳይሬክተር አቶ መሱድ ገበየሁ በበኩላቸው፣ ምርጫው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሰከነ ተሳትፎ የታየበትና ሰብአዊ መብቶችን ያከበረ እንደነበር ተናግረዋል።
የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች፣ ለነፍሰ ጡር እናቶች፣ ለወላጆችና አስተርጓሚ ለሚፈልጉ ዜጎች ምቹ እንዲሆኑ መደረጉን በመጥቀስ፤ ሂደቱ አካታችነትንና ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ስኬታማ ተግባር መሆኑን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል፣ በምርጫው ሂደት የታየው የወጣቶች ተሳትፎ ለዲሞክራሲ ሥርዓቱ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ወሳኝ መድረክ መሆኑም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ተወካይ አቶ አሌክሳንደር ንጉሤ እንደገለጹት፣ በሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ ወጣቶች ወደ ፊት የመጡበትና ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት በእጩነት የቀረቡበት የምርጫ ዘመን መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ይህም ወጣቱ የነገ ሀገር መረከብና ሀገርን ማጽናት እንደሚችል የታመነበት ትልቅ ስኬት መሆኑን አስገንዝበዋል።

በአጠቃላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ ሐሳባቸውን ለሕዝብ ባቀረቡበት ወቅት እንደ ባሕር በር ባለቤትነት ባሉ ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ያሳዩት ትብብርና የሰከነ የፖለቲካ ባህል ለዲሞክራሲ ግንባታ መሠረት የጣለ መሆኑ ተገልጿል።
ምርጫው በሁሉም መለኪያ ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዲሞክራሲ ጉዞ ትልቅ ስንቅ እንደሚሆን የሥራ ኃላፊዎቹ በቆይታቸው አረጋግጠዋል።
በወርቅነህ አቢዮ