AMN – ሰኔ 01/2018 ዓ.ም
የከተማ ልማት ከስነ-ምህዳር ጥበቃ ጋር በቅንጅት ሲመራ ምን ዓይነት ለውጥ ሊመጣ ይችላል? በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እየተተገበረ ያለው የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ለዚህ ጥያቄ በተግባር የተደገፈ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል።
መዲናዋ በዘላቂ ልማት እና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች በመታገዝ፣ የከተማዋን ሙቀት በመምጠጥ ንጹህ አየርን የምትጎናጸፍበት፣ የዘመናዊነትና የጤናማ ኑሮ ተምሳሌት ለመሆን በብርቱ እየገሰገሰች ነው።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአዲስ አበባ ገጽታ በአዲስ መልክ እየተቀየረ ይገኛል። ከአስፓልት መንገዶች ጎን ለጎን የሚዘረጉ ማራኪ አረንጓዴ ስፍራዎች እና ከቆሻሻ ማጠራቀሚያነት ወደ ስፖርትና መዝናኛ ማዕከልነት እየተቀየሩ ያሉ የወንዝ ዳርቻዎች ለከተማዋ አዲስ ትንፋሽ ሰጥተዋታል።
መዲናዋን ይሸት ከነበረ ወንዝ ወደ ለምለም አረንጓዴ መናፈሻ እየቀየረ ባለው የልማት ጉዞ ውስጥ የአረንጓዴ አሻራ ሚና በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

ይህ የከተማ ልማት እና የአረንጓዴ አሻራ ጥምረት፣ የአስፓልት መንገዶች የሚፈጥሩትን ከፍተኛ ሙቀት በመምጠጥ ከተማዋን ነፋሻማ ያደርጋታል።
ከተክሎች ጋር የተዋሃዱት የተስተካከሉ የእግረኛ መንገዶች ለከተማዋ ዓለም አቀፋዊ ገጽታን ሲያጎናጽፏት፣ በተሽከርካሪዎች የሚለቀቀውን ጋዝ በመቀነስ ረገድም የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።
አዲስ አበባ በውስጧ የሚያልፉ በርካታ ወንዞች ያሏት ከተማ ብትሆንም፣ ለረጅም ዘመናት እነዚህ ወንዞች የቆሻሻ መጣያ ሆነው መቆየታቸው ይታወሳል።
የወንዝ ዳርቻ ልማቱ አረንጓዴ አሻራን እንደ ዋነኛ መሣሪያ በመጠቀም፣ እነዚህን የወንዝ ዳርቻዎች ወደ መዝናኛ፣ ስፖርት መናፈሻ እና ውብ መተላለፊያ መንገዶች እየቀየራቸው ይገኛል።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በኮሪደር ልማት የተፈጠረውን የመንገድ ትስስር ከአረንጓዴ ኮሪደሮች ጋር በማገናኘት፣ ነዋሪዎች ያለምንም መስተጓጎል በእግር ወይም በብስክሌት የሚንቀሳቀሱበትን ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ነው።

በዚህም ሳቢያ የወንዝ ዳርቻዎች አሁን ላይ ለከተማዋ ነዋሪዎች የሰላም፣ የጤና እና የፈጠራ ማዕከል እየሆኑ መጥተዋል።
የአረንጓዴ አሻራን ከከተማ ልማት ጋር ማቆራኘት ፋይዳው ከውጫዊ ውበት የላቀ ነው። ይህ የኢኮኖሚ፣ የጤና እና የስነ-ምህዳር ዘላቂ ጥምረት ማሳያ ነው።
ዛሬ በኮሪደር ልማቱ አጠገብ የምንተክለው እያንዳንዱ ችግኝና የምናለማው እያንዳንዱ አረንጓዴ ቦታ፣ ነገ የምናገኘው የከተማችን ጤናማነት እና የነዋሪዎቿ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ መገለጫ ነው።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ