AMN- ሰኔ 2/2018 ዓ.ም

የጉምሩክ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና እንዳለው ተገለጸ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ24ኛ መደበኛ ስብሰባው የጉምሩክ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጀ ሪፖርት እና የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ ያቀረበ ሲሆን ረቂቅ አዋጁ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
አዋጁ በዘርፉ ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን የሚያስችል ሲሆን በጉምሩክ አሠራር ውስጥም ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነውም ብለዋል።

ረቂቅ አዋጁ በሀገሪቱ እያደገ የመጣውን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት የሚደግፍ እንዲሁም ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ መሆኑን አመላክተዋል።
አስመጪዎች በቀረጥና ታክስ አወሳሰን ላይ ያላቸውን አቤቱታ በማቅረብ ሂደት ያጋጥሟቸው የነበሩ የአሠራር መሰናክሎችን ለማስወገድ የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ያካተተ ረቂቅ አዋጅ መሆኑን ጠቁመዋል።

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ በኮንትሮባንድ ጭነት ምክንያት ተሽከርካሪ እንዲወረስ የሚያስችል ድንጋጌ ቢኖርም፣ ባለቤቱ በድርጊቱ ተሳታፊ ባልሆነበት ሁኔታ ንብረቱ ሊወረስ እንደማይገባም አንስተዋል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ የጉምሩክ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን፣ አዋጅ ቁጥር1425/2018 አድርጎ በሁለት ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡