AMN- ሰኔ 2/2018 ዓ.ም

በመጪው ክረምት ሊኖር የሚችል የኃይል መቆራረጥ ችግርን ለመቀነስና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ፡፡
በአገልግሎቱ የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ሥራ አስፈፃሚ ገበየሁ ሊካሳ (ዶ/ር ) በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አገልግሎቱ ለኃይል መቆራረጥ መንስኤ የሆኑ ችግሮችን በጥናት ከመለየት ባለፈ ያረጁ መስመሮችን የመተካት፣ አቅምን የማሳደግና በዋናው ግሪድና በፀሐይ ኃይል አማራጮች አዳዲስ መሰረተ-ልማቶችን የመገንባት ሥራዎችን በከፍተኛ ወጪ እያከናወነ ነው ብለዋል።
የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ እስካሁን በተከናወኑ የቅድመ-መከላከል ሥራዎች በአዲስ አበባ 1 ሺህ 750 ኪ.ሜ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ 62 ሺህ 274 ኪ.ሜ የሚሸፍን የመካከለኛ መስመር ፍተሻ ተደርጓልም ነው ያሉት።
በመሰረተ-ልማት ማስፋፋትና አቅም ማሳደግ ሥራ በሁለት መልኩ እየተከናወነ መሆኑን በማንሳት የመጀመሪያው በራስ ኃይል ፋይናንስ እና በሀገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የሚሰሩ ሥራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3 ሺህ 99 ኪ.ሜ የመካከለኛና ዝቅተኛ መስመር መልሶ ግንባታ እንደተከናወነ ጠቅሰው በ1 ሺህ 579 ነባር ትራንስፎርመሮች ላይ የአቅም ማሻሻያ ተደርጓል ብለዋል።
በተጨማሪም በከፍተኛ ጭነት ምክንያት የሚቋረጡ መስመሮችን ለመቀነስ ከ53 በላይ መጋቢ መስመሮችን የማመጣጠን፣ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ከ167 በላይ የስዊቺንግና ቁጥጥር መሣሪያዎችን የመትከል እንዲሁም በአዲስ አበባ የተበላሹ የመሬት ውስጥ ኬብሎችን የመጠገን ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በሚገኙ ብድሮች እና በዓለም አቀፍ ኮንትራክተሮች የሚሰሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፤ ከዚህ ቀደም ተጀምረው የነበሩት የሀረር፣ ወላይታ፣ ሻሸመኔ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጎንደርና ኮምቦልቻ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡
እንዲሁም የ10 ከተሞች የዲስትሪቢዩሽን ኔትወርክ መልሶ ግንባታ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ መግለጻቸውን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
መጪውን የክረምት ወቅት ተከትሎ ህብረተሰቡ በአንጻራዊነት የተሻለ የኃይል አቅርቦት እንዲኖረው ለማድርግ በሰፊው እየተከናወኑ ያሉና በዕቅድ የሚቋረጡ የፕሮጀክት ሥራዎችን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡