ከፋይዳ መታወቂያ እስከ መጀመሪያው የኤአይ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አስደማሚ የዲጂታል ሽግግር ጉዞ

You are currently viewing ከፋይዳ መታወቂያ እስከ መጀመሪያው የኤአይ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አስደማሚ የዲጂታል ሽግግር ጉዞ

AMN – ሰኔ 3/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከአርሶ አደሩ የዕለት ተዕለት ሥራ እስከ ፍርድ ቤት፣ ከመንገዶች መሠረተ-ልማት እስከ ዋና ዋና የመንግሥት ተቋማት ድረስ ያለውን አሠራር የሚያቀላጥፍና ዜጎችን ማዕከል ያደረገ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር በከፍተኛ ፍጥነት እየገነባች ነው።

ይህ ሀገራዊ የሽግግር ጉዞ በአሁኑ ወቅት “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” በተሰኘው ስትራቴጂ ሥር በትኩረት እየተመራ ይገኛል።

የሀገሪቱን የዲጂታል አቅም በማሳደግ ረገድ ቀዳሚውና ወሳኙ እርምጃ የሆነው የ“ፋይዳ” ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት እስከ አሁን ድረስ ከ41 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን መመዝገብ ችሏል።

ይህ ትልቅ ስኬት ለመንግሥት አገልግሎቶች መስተካከልና ለዲጂታል ኢኮኖሚው ዕድገት መፋጠን መሰረት የጣለ ሲሆን፣ ተቋማት የአገልግሎት ፈላጊዎችን ማንነት በፍጥነትና በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲያረጋግጡ ትልቅ በር ከፍቷል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሀገሪቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዘርፍ የአህጉሪቱ መሪ ለመሆን የምታደርገውን ጥረት በተግባር እያሳየች ትገኛለች።

የአፍሪካን የመጀመሪያ የኤአይ ኢንስቲትዩት ከመመሥረት ባለፈ በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የኤአይ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ እያካሄደች ትገኛለች፡፡

በሌላ በኩል ከመንግሥት ቢሮክራሲ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የዜጎችን እንግልት ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ሰፊ ሪፎርም ተደርጓል።

በዚህም መሠረት በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል እንዲዋሃዱ ተደርገው በኦንላይን ፖርታል፣ በኤሌክትሮኒክስ ክፍያና በወረቀት አልባ አሠራር እንዲሰጡ ተደርጓል።

ይህ የተዘረጋው ዘመናዊ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር ቀደም ሲል የነበረውን ረጅም ወረፋ፣ ቀጠሮ እና ጉዳይን ለማስፈጸም በአካል መገኘትን በማስቀረት ዜጎች ካሉበት ቦታ ሆነው በሞባይል መተግበሪያዎች ጭምር አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል።

አሠራሮቹ በቴክኖሎጂ በመመራታቸው ለአድልዎ እና ላልተገባ አሠራር የነበራቸውን ተጋላጭነት በእጅጉ የቀነሱ ሲሆን፣ የመረጃ አያያዝ ሥርዓቱም በዲጂታል ዳታቤዝ የተደራጀ በመሆኑ መረጃዎች እንዳይጠፉና ለፈጣን ውሳኔ አሰጣጥ እንዲያግዙ አድርጓል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኩል ይፋ የተደረገው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ይህ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ተቋማትን ከማዘመን ባለፈ የአርሶ አደሩን ምርታማነት የሚያሳድጉ የኤአይ ቴክኖሎጂዎች ላይ ጭምር ያተኮረ በመሆኑ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያፋጥን ነው፡፡

በቀጣይም የኢንተርኔት መሠረተ-ልማትን ይበልጥ ማጠናከርና የዜጎችን የዲጂታል ክህሎት ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ነዉ መረጃው የሚያመላክተው፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review