AMN- ሰኔ 3/2018 ዓ.ም
“አዲስ መሶብ” የአገልግሎት ማዕከላት የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ በሀገራችን የመጀመሪያ የሆኑ ዘመናዊ አሰራሮችን በይፋ ስራ ላይ አውለዋል።
በተለይም “ተንቀሳቃሽ መሶብ” የተሰኘው አዲስ አሰራር 8 ተቋማትን እና 41 መሰረታዊ አገልግሎቶችን ተንቀሳቃሽ በሆነ መልኩ ተደራሽ ማድረግ ችሏል።
ይህም ተገልጋዮች ሳይንገላቱ በሰፈራቸው ወይም በስራ ቦታቸው አካባቢ በእግረ መንገዳቸው እንዲገለገሉ ትልቅ አማራጭ መፍጠሩን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ደሳለኝ ተረፈ (ኢ/ር) ገልጸዋል።
በተጨማሪም በቴክኖሎጂ ዝግጅት ረገድ፣ ወጪን በከፍተኛ ደረጃ የሚቆጥብ እና ወጥነትን የሚያረጋግጥ የተዋሃደ የመሠረተ ልማት ሞዴል በተግባር ላይ ውሏል።

በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የለሙ 9 ዓይነት መሰረታዊ ሶፍትዌሮች በሁሉም ማዕከላት ስራ ላይ እንዲውሉ መደረጉንም አንስተዋል።
ማዕከላቱ አማራጭ የኃይል እና የኔትወርክ መስመር፣ የህፃናት ማቆያ፣ የሰራተኞች ካፌቴሪያ እና ዘመናዊ የደህንነት ካሜራዎች የተገጠሙላቸው በመሆናቸው ለአገልግሎት አሰጣጡ ጥራት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
በታምራት ቢሻው