AMN- ጥቅምት 17/2019 ዓ.ም
የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ፣ በኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አምባሳደር አብደላ ሀሰን አልሻምሲ ጋር በሁለትዮሽ ወታደራዊ እና ልማታዊ ትብብሮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ አቶ መሐመድ እድሪስ ሁለቱ ሀገራት በጋራ እየሠሩባቸው ባሉ የወታደራዊ መስኮች ላይ ያሏቸውን አጋርነቶች ያነሱ ሲሆን፣ በተለይም የመከላከያ ሚኒስቴር በልማት ድርጅቶቹ በኩል እያከናወናቸው በሚገኙ ውጤታማ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እያደረገች ያለውን ጉልህ አስተዋፅኦ እና ወሳኝ ድጋፍ አድንቀዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አምባሳደር አብደላ ሀሰን አልሻምሲ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያስመዘገበች ላለችው ፈጣን እና ሁለንተናዊ የልማት እድገት አድናቆታቸውን ገልፀው፣ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
አምባሳደሩ፣ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የልማት ድርጅቶች ጋር በቅንጅት መስራት መቻላቸውን እና ለተመዘገቡት ስኬቶችም እንደ እውነተኛ ስትራቴጂካዊ ወዳጅ ሀገር የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ በማበርከታቸው ትልቅ ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ብሔራዊ ጥቅሞቻቸው ላይ የተመሠረተ ጠንካራ የሁለትዮሽ ወዳጅነት የገነቡ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ ይህንን አጋርነት ወደ ላቀ እና ዘላቂ የወታደራዊ ትብብር ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት ለመስራት መስማማታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።