ስሟን እየሆነች ያለችው አዲስ አበባ

You are currently viewing ስሟን እየሆነች ያለችው አዲስ አበባ

AMN- ጥቅምት 19/2019 ዓ.ም

አዲስ አበባን እንደስሟ ለማድረግ በከተማ አስተዳደሩ የተተገበሩ የልማት ሥራዎች መዲናዋ ስሟን እንድትሆን እያስቻሏት ነው፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከተማዋ ያስመዘገበችው ፈጣን ለውጥ የነዋሪዎቿን የዕለት ተዕለት ሕይወት ቀይሯል ፣ የመዲናዋን ገጽታ በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ አድርጎታል። ይህ ትልቅ ለውጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የፌዴራል መንግሥት በቁርጠኝነት እና በስትራቴጂያዊ እቅድ የመሩት የልማት ማዕበል ውጤት ነው።

የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ ከቀየሩት ዋና ዋና ልማቶች መካከል የመዲናዋ ዋና ዋና መንገዶች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መተላለፊያዎች እና አረንጓዴ ሥፍራዎች ተገንብተዋል ፣ የተጎሳቆሉት በዘመናዊ መልኩ ታድሰዋል።

ይህ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ውበት ከማጎልበት ባሻገር ለነዋሪዎች ጤናማ እና ምቹ አካባቢን ፈጥሯል። ዘመናዊ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ተደራሽነት በመሻሻሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ፍሰት ፈጣን እና ቀልጣፋ ሆኗል።

እንደ እንጦጦ ፓርክ፣ ሉሲ እና ሸገር ፓርኮች ያሉ ሰፊ አረንጓዴና መዝናኛ ቦታዎች መገንባታቸው አዲስ አበባን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ አድርገዋታል። ቢሮክራሲን በማቅለል እና አገልግሎትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመደገፍ የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ፍትሃዊ፣ ፈጣን እና ግልጽ እንዲሆን ተደርጓል።

የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ታላላቅ ፕሮጀክቶች ከሐሳብ ወደ መሬት በማውረድ ረገድ ወሳኝ አፈጻጸም አሳይቷል፡፡ በዚህም አስተዳደሩ የከተማዋን ነባር ችግሮች በመለየት እና ፈጣን መፍትሄዎችን የሚሹ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሷል።

የከተማዋን ውስጣዊ ገቢ በማሳደግ እና በባለድርሻ አካላት መካከል ትብብር በመፍጠር ለልማት የሚሆን በቂ ፋይናንስ ማስተባበር ችሏል። ልማቱ የነዋሪዎችን ቀጥተኛ ተሳትፎ ያካተተ በመሆኑ ሕዝቡ የልማቱ ባለቤት ሆኖ እንዲሰማው አድርጓል።

አዲስ አበባ ዛሬ የምታሳየው ፈጣን ለውጥ የዕቅድ፣ የቁርጠኝነት እና የአስተዳደር ውጤት ነው። የከተማ አስተዳደሩ የተቀናጀ ጥረት ከተማዋን በእርግጥም እንደ ስሟ አዲስ የሚያደርጓት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረቶች ተጥለዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review