AMN- ጥቅምት 19/2019 ዓ.ም
አዲስ አበባ የአፍሪካን አራተኛውን የግሉ ዘርፍ የመፈናቀል ፎረም ከኅዳር 7 እስከ 9 ቀን 2019 ዓ.ም ልታስተናግድ መሆኑ ተገለጸ።
በፎረሙ ከንግዱ፣ ከመንግሥት፣ ከፋይናንስና ከሰብዓዊ ድጋፍ ዘርፎች የተውጣጡ ተወካዮችን እንዲሁም በመፈናቀል የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች ይሳተፉበታል፡፡ የተፈናቀሉ ወገኖች በኢኮኖሚው ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ የሥራ ዕድልን፣ ኢንቨስትመንትንና የንግድ ሥራ ልማትን ማስፋፋት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ተመላክቷል።
በአማሆሮ ኮሊሽን፣ ኢንኮሞኮ እና በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ (UNHCR) አዘጋጅነት፣ ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የሚካሄደው ፎረም፣ በመፈናቀል የተጎዱ ሰዎች በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲሳተፉ የሥራ ዕድልን፣ ኢንቨስትመንትንና የንግድ ሥራ ልማትን ማስፋፋት ላይ እንደሚያተኩርም ተገልጿል። የአማሆሮ ኮሊሽን መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአፍሪካ ከ45 ሚሊዮን በላይ በግዳጅ የተፈናቀሉ ሰዎች ይገኛሉ።
እነዚህ ዜጎች በዓመት እስከ 27 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ እንደሚያመነጩና ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የሚጠጉ የንግድ ሥራዎችን እንደሚያንቀሳቅሱ በጥናቱ ተመዝግቧል። ኢትዮጵያ በበኩሏ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን፣ እንዲሁም ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ በውስጥ ሀገር የተፈናቀሉ ዜጎችን እያስተናገደች ትገኛለች።
ሀገሪቱ እነዚህ ዜጎች ተገቢውን የሥራ ዕድል እንዲያገኙ፣ የራሳቸውን ንግድ እንዲመሠርቱ እና የፋይናንስ አገልግሎቶችን በበቂ ሁኔታ እንዲጠቀሙ የሚያስችሉ አበረታች ማሻሻያዎችን እያደረገች ትገኛለች።

ይህ ዓለም አቀፍ ፎረም በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) አፍሪካ አዳራሽ እና በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የሚካሄድ ይሆናል። በዝግጅቱም ወቅት የተፈናቀሉ ሰዎችና የአካባቢ ማኅበረሰቦች ያቋቋሟቸው የንግድ ድርጅቶች ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን የሚያሳዩበት እንዲሁም የሚሸጡበት ልዩ መድረክ እንደሚኖር ተገልጿል።
ይህ መድረክ ከዚህ ቀደም በ2021 ዓ.ም. በኪጋሊ (ሩዋንዳ)፣ በ2023 ዓ.ም. በአክራ (ጋና) እና በ2025 ዓ.ም. በናይሮቢ (ኬንያ) ከተካሄዱት ዓለም አቀፍ ዝግጅቶች ልምድ በመውሰድ፣ በዚህኛዉ ዓመት በአፍሪካ የሥራ ዕድልን፣ ኢንቨስትመንትንና የንግድ ትብብርን ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል።
በአናንያ ንጉሡ