AMN- ጥቅምት 20/2019 ዓ.ም
የ2018 የግብር ዘመን የደረጃ “ሀ” ዓመታዊ የንግድ ትርፍ የማሳወቂያና የመክፈያ ጊዜ ጥቅምት 30 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡
በዚህም ግብር ከፋዮች የመጨረሻ ቀናትን ሳይጠብቁ ግብራቸውን አሳውቀው በወቅቱ እንዲከፍሉ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለኤ ኤም ኤን እንደተናገሩት፤ የደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋዮች የንግድ ትርፍ የማሳወቂያና የመክፈያ ጊዜው እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡
የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የግብር ማሳወቂያና መክፈያ ጊዜ ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ አብዛኞች ግብር ከፋዮች የግብር ግዴታቸውን በወቅቱ መወጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች ደግሞ ከሐምሌ 1 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ እንዲያሳውቁና እንዲከፍሉ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ቢሮው ከ2018 ዓም ጀምሮ ወራዊ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) እና ደሞዝ የማሳወቅና ክፍያ የመፈጸም ተግባርን ሙሉ በሙሉ በኦንላይን ማድረጉን የገለፁት አቶ ሰውነት፤ ከ2019 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮችን ዓመታዊ የንግድ ትርፍ ግብር የማሳወቅና የመክፈል ሂደት ሙሉ በሙሉ በበይነ-መረብ (ኦንላይን) እንዲሆን መደረጉን አስረድተዋል።
በዚህም መሰረት ግብር ከፋዮች በአካል ወደ ቢሮ መምጣት ሳይጠበቅባቸው የሂሳብ መዝገቦቻቸውን በሲስተም ከማስገባት ባሻገር አስፈላጊ ሰነዶችን ቃለ መሐላ በፈጸሙበት የኢሜይል አድራሻ መላክ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የኦዲት ስራው ተከናውኖ የክፍያ ማዘዣ በሲስተሙ ሲላክላቸውም ባሉበት ሆነው ክፍያቸውን በኦንላይን መፈጸም የሚጠበቅባቸው ሲሆን ግብር ከፋዩ በአካል መምጣት የሚጠበቅበት በኦንላይን ለፈፀመው ክፍያ ደረሰኝ ለማወራረድ ካሸሪ ጋር ብቻ እንደሆነ ተጠቁሟል።
አሰራሩ ከዚህ ቀደም ይነሱ የነበሩ የግብር ከፋዮች እንግልት፣ ወረፋና ምልልስ በመቅረፍ የግብር ከፋዮችን በአገልግሎት አሰጣጥ የነበሩ ቅሬታዎችን ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ ታስቦ የተዘረጋ እንደሆነም አቶ ሰውነት ገልጸዋል።
በመሆኑም ግብር ከፋዮች በመጨረሻዎቹ ቀናት ከሚያጋጥሙ የሲስተም መጨናነቅ፣ ወረፋና መጉላላት እንዲሁም በወቅቱ ባለመክፈል ከሚመጣ ቅጣት ለመዳን ቀሪዎቹን ጥቂት ቀናት በመጠቀም በኦንላይን አሳውቀው በኦንላይን እንዲከፍሉ መልእክት ተላልፏል።
በሸዋየ ከፍያለ