AMN – ኅዳር 19/2019 ዓ.ም
የከተማዋ ወጣቶች ያላቸውን የተለያዩ የኪነ ጥበብ ሞያዎችን ተጠቅመው የመዲናዋን ለዉጥ የሚተርኩና የሚያስታውሱ ሊሆኑ እንደሚገባ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃፍታይ ገ/እግዚአብሔር ገለጹ።
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጋራ ሆነው ያዘጋጁት የ«አዲስ ታለንት ሾው» ሁለተኛ ምዕራፍ መርሃ ግብር «ጥበብ ለኢትዮጵያ ልእልና» በሚል መሪ ሃሳብ በአድዋ ድል መታሰቢያ ተጀምሯል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃፍታይ ገ/እግዚአብሔር በመዲናዋ የሚገኙ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች ችሎታቸውን በአደባባይ እንዲያሳዩ ምቹ ምኅዳር መፍጠር የቢሮው ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ታለንት ሾው የተሰጥኦ ውድድርም በየአካባቢው የተደበቁ የጥበብ ክህሎቶችን በማውጣት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።
ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ይህ መርሐ ግብር፣ ወጣቶች በግጥም፣ በሙዚቃ፣ በሥዕልና በሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎች ራሳቸውን እንዲገልጹና ሙያቸውን እንዲያሳድጉ ዕድል እንደሚሰጥም አብራርተዋል።

አዲስ አበባ እያከናወነቻቸው ባሉ የኮሪደርና የከተማ ውበት ልማቶች ዓለም አቀፍ የኮንፈረንስና የቱሪዝም ማዕከል እየሆነች መምጣቷንም ኃላፊው ተናግረዋል።
ይህንን የከተማዋን ፈጣን ለውጥና የሕዝቡን የበለጸገ ባህል ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ለማስተዋወቅ የወጣቶች የጥበብ ሥራዎች ቁልፍ መሣሪያ መሆናቸውን ገልጸው፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮው ለመድረኩ መሳካትና ለተወዳዳሪ ለወጣቶች መብቃት የሚያደርገውን ተቋማዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በአስማረ መኮንን