የሰውና የተፈጥሮ መስተጋብር የተሰናሰለባት ከተማ አዲስ አበባ!

You are currently viewing የሰውና የተፈጥሮ መስተጋብር የተሰናሰለባት ከተማ አዲስ አበባ!

AMN – ኅዳር 19/2019 ዓ.ም

በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የልማት ሥራ ከኮንክሪት ጫካ ወደ ውብ አረንጓዴ ከተማ የሚደረግ ታሪካዊ ሽግግር ነው፡፡

የአንድ ዘመናዊ ከተማ ውበትና ስኬት የሚለካው በሰማይ ጠቀስ ህንጻዎችና በተዘረጉለት የአስፋልት መንገዶች ብቻ ሳይሆን፣ ነዋሪዎች ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው መኖር የሚችሉባቸውን አረንጓዴ ስፍራዎች በማካተት ጭምር ነው።

በቅርብ ዓመታት በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉት የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻዎች ልማት እና የከተማ መልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች ይህንኑ ዓለም አቀፍ መርህ በተግባር ያረጋገጡ የልማት አሻራዎች ናቸው።

ለዓመታት የአዲስ አበባ የከተማ ዕድገት ከተፈጥሮ ይልቅ ወደ ኮንክሪት ግንባታ ያደላ ነበር። የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋንም 2.8 በመቶ ድረስ አሽቆልቁሎ ነበር።

በዚህም ነዋሪዎች ንጹህ አየር የሚያገኙባቸውና ቤተሰቦቻቸውን ይዘው የሚዝናኑባቸው ስፍራዎች እጅግ ውስን ነበሩ።

ይሁን እንጂ፣ በተቀናጀ መልኩ የተካሄደው የወንዝ ዳርቻዎችን የማልማት ሥራ እንዲሁም የህዝብ ፓርኮችና የአትክልት ስፍራዎች ልማት ይህንን ታሪክ ቀይሮታል። ዛሬ ላይ የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋን ወደ 25 በመቶ ማደግ ችሏል።

ይህ ዕድገት አዲስ አበባን የአየር ንብረት ብክለትን የምትቋቋም፣ የሙቀት መጠኗ የተመጣጠነ እና ከተፈጥሮ ጋር ተስማምታ የምትኖር ውብ አረንጓዴ ከተማ እንድትሆን ትልቅ መሰረት ጥሏል።

የኮሪደር፥ የወንዝ ዳርቻ እና የመልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች መንገዶችን ከማስፋት ባለፈ፣ በየመንገዱ ዳር የተተከሉ የዛፍ ጥላዎችን፣ የእግረኛ መንገዶችንና ውብ የአረንጓዴ ስፍራዎችን በስፋት አካተዋል።

ይህ የተቀናጀ ልማት ለከተማዋ ነዋሪዎች የማህበራዊ ትስስር ማዕከላት መሆን ችለዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች እንደቀድሞው «የት ሄጄ ንጹህ አየር እየተነፈስኩ ልዝናና?» የሚል ጭንቀት የለባቸውም።

ዛሬ የመዝናኛ አማራጮች ተበራክተዋል ጽዱ፣ ውብ እና ደህንነታቸው የተጠበቀ በርካታ የህዝብ ፓርኮች በየአካባቢው ለምተዋል።

በእነዚህ ስፍራዎች ሳምንቱን ሙሉ ቀንም ሆነ ምሽት ወጣቶች፣ አረጋውያን እንዲሁም ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በመሆን ጊዜያቸውን ማሳለፍ አዲስ የከተማ ባህል ሆኗል።

ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለሚያደርጉትም ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን የነዋሪዎችን ማህበራዊ ትስስርና አብሮነት ይበልጥ እያጠናከረ ይገኛል።

አዲስ አበባ አሁን የደረሰችበት የ25 በመቶ የአረንጓዴ ሽፋን ትልቅ ስኬት ቢሆንም፣ የከተማ አስተዳደሩ ዓለም አቀፉ 30 በመቶ የከተሞች ዝቅተኛ የአረንጓዴ ሽፋን መስፈርት የሆነውን ለማሳካት በትጋት እየተሰራ ይገኛል።

ከመቼውም ጊዜ በላይ የልማት ፍጥነትና የህዝቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ይህንን ግብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሳካት እንደሚቻል ምንም ጥርጥር የለም።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው ልማት ለዛሬው ትውልድ ምቹ ከተማን መፍጠር፡ የመዝናናትና የንጹህ አየር ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ፣ ለመጪው ትውልድ መሰረታዊ ሚዛኗን የጠበቀች፣ ዘላቂና ለኑሮ ምቹ የሆነች ከተማን የማስረከብ ታላቅ ራዕይ አካል ነው። መረጃው የከንቲባ ጽ/ቤት ነው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review