AMN- ኅዳር 20/2019 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 91ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በማሥመልከት ቢሾፍቱ ከተማ ያዘጋጀው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ፣ በወንዶች ቢኒያም መላክ ከሸገር ሲቲ በሴቶች ደግሞ አዳኑ ሄንቆ ከሸገር ሲቲ አሸናፊ በመሆን ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ለውድድሩ አሸናፊዎች እንኳን ደስ አላችሁ በማለት፣ የአየር ኃይልን የ91ኛ ዓመት የድል ጉዞ በማሰብ በተደረገው ጥሪ የመጣችሁ በሙሉ እናመሰግናለን ብለዋል።
አዛዡ አየር ኃይል የሀገርን ዳር ድንበርና የአየር ክልል እያስጠበቀ የቢሾፍቱ ከተማ ሁሉ አቀፍ የልማት ስራዎች ላይም ከፊት ሆኖ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንን ታሪካዊ በአል ከህብረተቡ ጋር ማክበር ትልቅ ትርጉም አለው ሲሉም ገልፀዋል።

የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መኪዮ መሀመድ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ የጀመረው ከፀጥታ ተቋማት መሆኑን አስታውሰው፣ 91 ዓመታትን ያስቆጠረው አየር ኃይል ይህን ታሪክ ለማስቀጠል እየሰራ ያለና ወንድማማችነትን ለማጠናከር ትልቁን ድርሻ እየተወጣ የስፖርት ዘርፍን እየደገፈ ይገኛል ብለዋል።
በውድድሩ በወንዶች ቢኒያም መላክ ከሸገር ሲቲ 1ኛ ደረጃን በመያዝ የወርቅ ሜዳሊያና የ500 ሺህ ብር እንዲሁም በሴቶች አዳኑ ሄንቆ ከሸገር ሲቲ 500 ሺህ ብርና የወርቅ መዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።

በወንዶች 2ኛ ሙሲን ሀጂ ከሸገር ሲቲ 3ኛ ጭንቢሳ ደበሌ ከሸገር ሲቲ አሸናፊ ሲሆኑ፣ በሴቶች 2ኛ ቢቄሌ አንበሶ ከኦሮሚያ ፓሊስ 3ኛ ቤቴሊሔም አለና ከሸገር ሲቲ አሸናፊ በመሆን 2ኛ ደረጃ የያዙ የ250 ሺህ ብር 3ኛ ደረጃ የያዙ የ150 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል።
የውድድሩ አሸናፊዎች አየር ኃይል ባዘጋጀው የጎዳና ላይ ሩጫ ማሸነፋቸው የፈጠረባቸው ደስታ የተለየ መሆኑን ጠቅሰው “አየር ኋይል መመኪያችን” ነው ሲሉም መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።