አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ህብረተሰቡ ዘመኑ የደረሰበትን የላቀ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኝ መረጃ ከመስጠት ረገድ የጀመረዉን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል

AMN- ሰኔ 2/2018 ዓ.ም

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ህብረተሰቡ ዘመኑ የደረሰበትን የላቀ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኝ መረጃ ከመስጠት ረገድ የጀመረዉን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ዲባባ ገለጹ፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና ስኬት ባንክ በትብብር መስራት በሚችሉባቸዉ ጉዳዮች ዙሪያ ዉይይት በማካሄድ የስራ ስምምነት አድርገዋል፡፡

በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና መስሪያቤት በተደረገዉ ዉይይት ላይ ከባንኩ ሌሎች አመራሮች ጋር የተገኙት የስኬት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ዳምጠው አለማየሁ፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከጊዜ ወደጊዜ አቀራረቡን እያዘመነ እና እያሰፋ መምጣቱን በመግለጽ ይህንኑ ዕድል በመጠቀም ባንኩ ከኤኤምኤን ጋር አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ባንኩ የሚሰጣቸዉን የፋይናንስ አገልግሎቶች በሚገባ ተደራሽ ለማድረግ እና የሚዲያ ተቋሙም የተለያዩ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ከስኬት ባንክ በሚያገኝበት ሁኔታ ላይ ከስምምነት መድረሳቸውንም የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ዳምጠው አለማየሁ ጨምረዉ ተናግረዋል፡፡

ስኬት ባንክ በመዲናዋ ከ750 ሺህ የሚበልጡ ደንበኞቹ ጋር ለመድረስ በይበልጥ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ተቀራርቦ መሥራቱ ጠቃሚ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰለሞን ዲባባ በበኩላቸው፣ ሁለቱም ተቋማት የከተማ አስተዳደሩ እንደመሆናቸው መጠን፣ የከተማውን ህዝብ የማገልገል ተመሳሳይ ራዕይ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ስኬት ባንክ በፋይናንስ በኩል አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ደግሞ የባንኩን አገልግሎቶች ወደ ህዝብ በማድረስ ረገድ በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን ያነሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ ይህ ስምምነት የሁለት ባለ ራዕዮች ስምምነት አድርገው እንደሚወስዱት ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ሦስተኛዋ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማዕከል እንደመሆኗ፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና ስኬት ባንክ ለዚህ ከፍታ በርካታ ሥራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸውንም ተናግረዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ህብረተሰቡ ዘመኑ የደረሰበትን የላቀ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኝ በቴሌቪዥን፤ በሬድዮ፤ በዲጂታል ሚዲያና በአዲስ ልሳን ጋዜጣ አመራጮቹ መረጃ ከመስጠት ባለፈ ህብረተሰቡ በፈጠራ የታገዘ ጠንካራ የስራ ባህል እንዲኖረዉ ከማድረግና የቁጠባን ባህል ከማስረጽ ረገድ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review