AMN – ነሐሴ 21/ 2018 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው “የሚክስድ ማርሻል አርት እና የንኪኪ ስፖርት በአንድ መድረክ የሚይዘው ዓድዋ ፋይት ናይት” ውድድር፣ በታሪካዊው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በመገኘት ወጣቶችን አበረታተዋል።

ከንቲባዋ በመልእክታቸው፥ ውድድሩ በአደጉና በበለፀጉ ሀገራት እጅግ ተወዳጅ ስፓርት ሲሆን፤ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፓርት መሰረተ ልማቶችን የሚፈልግ በመሆኑ እስከ አሁን በአገራችን ሲካሄድ አይስተዋልም፥ ዛሬ ግን በከተማችን በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ምቹ የስፓርት መሰረተ-ልማቶች እውን በመሆናቸው አዳዲስ የስፓርት አይነቶች እየተካሄዱ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

ውድድሩ ወጣቶች ልዩ ተሰጥኦና ችሎታቸውን የሚያዳብሩበት ፣ለስፖርት ቱሪዝም፥ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መስተጋብር የሚጠናከርበት፣ የከተማችንን ገፅታ የሚቀይር እና ተወዳዳሪነታችንን የሚጨምር ነው ብለዋል።
እንዲህ አይነት ውድድሮች፥ ወጣቱን ታሳቢ ያደረጉ መሠረተ-ልማቶችን ይበልጥ አጠናክረን እንድንሰራ ያደርገናል፤ ወጣቱም አለማቀፍ የተወዳዳሪነት መንፈስ እንዲያሳድግ ዕድል ይሰጣል ሲሉ ገልፀዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልዕክታቸው አዘጋጆችን “በርቱ” ያሉ ሲሆን፤ ለተወዳዳሪዎችም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።