የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብፁዓን አባቶች በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ ጉብኝቱን አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ ከጉብኝት በኋላ በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው በተለያዩ ከተማ አቀፍ ጉዳዮች እና የጋራ ስራዎች ዙሪያ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ብፁዓን አባቶች ከለውጡ ጀምሮ በከተማዋ መንግሥት ያከናወናቸውን የልማት ስራዎች በመጐብኘት ለተሰሩት ስራዎች ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸውን ያስታወቁት ከንቲባዋ በቀጣይ ጊዜያትም ፈጣሪ ክንውንን እንዲሰጠን በፀሎት እና በቡራኬ እንደማይለዩን ገልጸውልናል ነው ያሉት።
“እኛም የሀገራችን ብቻ ሳይሆን የአህጉራችን መዲና እና የዓለም አቀፉ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ መናገሻ የሆነች አዲስ አበባችንን ይበልጥ ለመለወጥ ያለንን ቁርጠኝነት እየገለጽን፣ አባቶቻችን በምክር እና ጸሎት ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ስላሉ እና ስላበረታቱን ከልብ እናመሰግናለን” ሲሉም ገልጸዋል።