AMN-ሰኔ 29/2018 ዓ.ም
የ23ኛ የዓለም ዋንጫ የጣምራ አዘጋጅ አሜሪካ በ32ቱ የማጣሪያ ዙር ቦስኒያን ስታሸንፍ ወሳኝ አጥቂው ፎላሪን ባሎጎን በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቶ ነበር።
አሜሪካ ጨዋታውን 2ለ0 ብታሸንፍም ቀይ ካርዱ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ አልፏል። ተጫዋቹ በቅጣቱ አንድ ጨዋታ እንደሚያመልጠው ቢነገርም ፊፋ ቅጣቱን ማራዘሙን አስታውቋል።
ፊፋ የስነምግባር መመሪያ አንቀፅ 27 ተጠቅሜ ነው ውሳኔውን ያሳለፍኩት ቢልም ከየቦታው የሰላ ትችት እየደረሰው ይገኛል። ውሳኔው እንደተሰማ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፊፋ ፍትሃዊ ያልሆነውን ውሳኔ በመቀልበሱ አመሰግናለሁ ብለው ነበር።

ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ እና የቡድን አባላቱ በውድድሩ ሦስት ግቦችን ያስቆጠረው ተጫዋች ዛሬ ከቤልጂየም ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ እንደሚሰለፍ ሲያውቁ ደስታቸው ከፍ ብሏል።
ኒውዮርክ ታይምስ እንደፃፈው ዶናልድ ትራምፕ ቀጥታ ለጂያኒ ኢንፋንቲኖ ደውለው ቅጣቱ እንዲነሳ ጠይቀው እንደነበር ይፋ አድርጓል።
የቤልጂየም እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጉዳዩ የተሰማውን ቅሬታ በደብዳቤ አስታውቋል። የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሩዲ ጋርሺያም ውሳኔውን “ትልቅ ፌዝ” ብለውታል።
ከመከናወኑ በፊት ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ ያገኘው የአሜሪካ እና ቤልጂየም ጨዋታ ለሊት 9፡00 ይጀምራል።
በሸዋንግዛው ግርማ