AMN- ሐምሌ 1/2018 ዓ.ም
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጦርነት አውዳሚ እንጂ ወደ እውነተኛ ድል እንደማይመራ በተግባር ያሳየ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላምና ደህንነትን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የተለመደውን የአሸናፊና ተሸናፊ የፖለቲካ ስሌት የቀየረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
መንግሥት ወታደራዊ የበላይነት በነበረው ወቅት ጭምር ወንድማማቾች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው እንዲወያዩ ማድረጉ፣ ለዘላቂ ሰላም ያለውን ፅኑ ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት መድረክ እንደነበርም ገልጸዋል።

የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በትግራይ ክልል ሰላማዊ እንቅስቃሴን የሚያረጋግጥና አካባቢውን የሚያስተዳድር ጊዜያዊ አስተዳደር በስኬት መቋቋሙን አስታውሰዋል።
በስምምነቱ መሠረት ከ60 ሺህ ያላነሱ የታጠቁ ኃይሎች አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓልም ብለዋል።
በጦርነቱ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ተቋርጠው የነበሩት የአየር ትራንስፖርትና የቴሌኮም አገልግሎቶች እንደገና እንዲቀጥሉ የተደረገ ሲሆን፣ የነበረው ሀብትና ንብረትም ተጠብቆ እንዲቆይ መደረጉን አስታውሰዋል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት ሰላም የሁልጊዜም አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አሁንም ግን በትግራይ ክልል የሚታዩ አዳዲስ ውጥረቶች እንዲሁም የክልሉን ሰላም ለማደናቀፍ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንደሚስተዋሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
የትግራይ ክልልን ጨምሮ በየአካባቢው ያሉ ታጣቂዎች ከጦርነት አውዳሚነት በመማር የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉና በሀገር ግንባታ ሂደት ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በበረከት ጌታቸው